በኢትዮጵያ ከሰሞኑ ከተከሰቱት የመሬት መንቀጥቀጦች ከፍተኛ የሆነው እና በሬክተር ስኬል 5.5 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ዛሬ አርብ ምሽት መከሰቱን የአሜሪካ እና የአውሮፓ ተቋማት አስታወቁ። የመሬት መንቀጥቀጡ በአፋር ክልል አዋሽ አካባቢ የተከሰተው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ነው።
ይህ ርዕደ መሬት ከአዋሽ ከተማ 44 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራ የደረሰ መሆኑን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታውቋል። የአውሮፓ ሜዲትራንያን ሴይስሞሎጂ ማዕከል (EMSC) በበኩሉ የመሬት መንቀጥቀጡ ከጭሮ ከተማ 54 ኪሎ ሜትር፣ ከአዳማ ከተማ ደግሞ በ152 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ የደረሰ መሆኑን ገልጿል።
የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል በበኩሉ ምሽቱን የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 5.0 የሚለካ እንደሆነ በመረጃ ቋቱ ላይ በመጀመሪያ ቢያስፍርም፤ ሰዓታት ዘግይቶ መጠኑን ወደ 5.4 አስተካክሎታል። ይህ የምርምር ማዕከል ከሁለቱ ተቋማት በተለየ፤ ትላንት ሐሙስ ለሊት በአፋር አካባቢ በሬክተር ስኬል 5.3 የደረሰ ርዕደ መሬት መከሰቱን አስታውቆ ነበር።
በህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 መጠን ያላቸው ናቸው
ሶስቱም ተቋማት ዛሬ አርብ አመሻሽ 11 ሰዓት ተኩል ገደማ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ ግን የመዘገቡት በተመሳሳይ መጠን ነው። በዚህ ጊዜ የተመዘገበው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 5.2 የተለካ ነው። ከ2.5 እስከ 5.4 በሬክተር ስኬል የመለኪያ መሳሪያ የሚመዘገቡ የመሬት መንቀጥቀጦች “ንዝረታቸው ሊሰማ የሚችል ነገር ግን አነስተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ” መሆናቸውን በክስተቶቹ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ይገልጻሉ።
በህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 መጠን ያላቸው ናቸው። በአፋር ክልል በገቢ ረሱ ዞን፤ ዱለሳ ወረዳ፣ ድሩፉሊ ቀበሌ ባለፈው ሰኞ ለሊት በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከ20 በላይ ቤቶች እና ሱቆች መፍረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወረዳው አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር።
በቀጣይ ቀናት በነበሩ የመሬት መንቀጥቀጦች ተጨማሪ ቤቶች ላይ ጉዳት መከሰቱን የወረዳው አስተዳዳሪ በዛሬው ዕለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]