ከአማራ ክልል ተማሪዎች 60 በመቶ የሚጠጉት “ከትምህርት ገበታ ውጭ” መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ

በቤርሳቤህ ገብረ

በአማራ ክልል ከሚገኙ ተማሪዎች ውስጥ 59.8 በመቶ የሚሆኑት፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን “ከትምህርት ገበታ ውጭ” መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ተናገሩ። በክልሉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል 32 በመቶ የሚሆኑት ከመማር ማስተማር ተልዕኮዋቸው “መስተጓጎላቸውንም” ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

አቶ አረጋ ይህንን ያሉት፤ ትላንት ማክሰኞ የካቲት 4፤ 2017 ዓ.ም በተጀመረው እና ዛሬም በቀጠለው የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው። አቶ አረጋ በዚሁ ሪፖርታቸው ካነሷቸው ጉዳይ መካከል በክልሉ ያለውን የትምህርት ሁኔታ የተመለከተው ይገኝበታል።

በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት “በተጨባጭ በመማር ማስተማር ሂደት እየተሳተፉ” የሚገኙ ተማሪዎች ብዛት 2.78 ሚሊዮን እንደሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጠቅሰዋል። ይህ አሃዝ በክልሉ በትምህርት ገበታቸው ላይ ሊገኙ የገባቸው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 40.2 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ብቻ የሚሸፍን እንደሆነም አቶ አረጋ አስረድተዋል። 

“ቀሪ 59.8 በመቶ የሚሆነው ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆኑን ለተከበረው ምክር ቤት ማስረዳት ያስፈልጋል” የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በትላንቱ ጉባኤ ውሎ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። በአማራ ክልል በዘንድሮው በጀት ዓመት ለመመዝገብ ታቅዶ የነበረው አጠቃላይ የተማሪዎች ብዛት 7.1 ሚሊዮን እንደሆነ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ ከሶስት ሳምንት በፊት የቢሮውን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም በገመገሙበት ወቅት፤ በዚህ ዓመት ከተመዘገቡ የክልሉ ተማሪዎች ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ የሚሆኑት “ትምህርታቸውን መማር እንዳልቻሉ” ተናግረው ነበር። እነዚህ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ያልቻሉት፤ በክልሉ ባለው “ጦርነት” እንዲሁም በተማሪዎች እና በመምህራን ላይ በሚደርስ “እንግልት እና ጫና” ምክንያት መሆኑን የቢሮ ኃላፊዋ በወቅቱ ገልጸዋል። 

በክልሉ ምክር ቤት መደበኛ መክፈቻ ላይ በትላንትናው ዕለት ንግግር ያደረጉት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፤ የትምህርት ዘርፉ የገጠመውን ይህንኑ ተግዳሮት አስተጋብተዋል። አፈ ጉባኤዋ በዚሁ ንግግራቸው፤ በክልሉ ባለው “የጸጥታ ችግር”፣ ትምህርት እንዳይጀመር ተደረገ ባሉት “አሉታዊ ቅስቀሳ” እንዲሁም “በየደረጃው ባለ የመፈጸም እና የማስፈጸም ችግር” ሳቢያ “በርካታ ተማሪዎች” ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“እውነት ለመናገር በጣም ያማል። በልጆቻችን ላይ የተጋረጠ አደጋ እና ትልቅ ጠባሳ ነው። የወላጅ አንገትንም ያስደፋል። የትምህርት ተከታታይነትም አደጋ ላይ የጣለ ነው”

– ፋንቱ ተስፋዬ፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

“እውነት ለመናገር በጣም ያማል። በልጆቻችን ላይ የተጋረጠ አደጋ እና ትልቅ ጠባሳ ነው። የወላጅ አንገትንም ያስደፋል። የትምህርት ተከታታይነትም አደጋ ላይ የጣለ ነው። በጥቅሉ የህጻናት የመማር መብትን የደፈጠጠ፣ በህዝባችን በገዛ ልጆቹ እየተፈጸመ ያለ፣ ትውልድን የማንቀራጨት ማሳያ ነው” ሲሉ አፈ ጉባኤዋ የሁኔታውን አሳሳቢነት ለክልሉ ምክር ቤቱ አስገንዘበዋል። 

በአማራ ክልል ያሉ አብዛኛዎቹ የትምህርት ተቋማት “ከደረጃ በታች” እንደነበሩ በንግግራቸው ያስታወሱት ፋንቱ፤ ባለፉት ዓመታት በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋማቱ “ከፍተኛ ውድመት” ማስተናገዳቸውን አስረድተዋል። ይህም ክልሉ በሚያከናወነው የማህበራዊ ልማት ስራ ላይ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል” ሲሉ አክለዋል። 

በክልሉ ያሉ የትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ በርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት ላይ ተነስቷል። በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት መደበኛ የመማር ማስተማር ተግባራቸውን ያከናወኑ ትምህርት ቤቶች ብዛት 7,444 መሆኑን አቶ አረጋ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። 

ፎቶ፦ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

በአማራ ክልል ያሉት ትምህርት ቤቶች ብዛት 10,983 ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አሁን በስራ ላይ ያሉት 67.7 በመቶው ብቻ መሆናቸው በሪፖርቱ ይፋ ተደርጓል። አቶ አረጋ “3,466 የሚሆኑት ወይንም 32 በመቶ በሚሆኑት ትምህርት ቤቶች፤ ከመማር ማስተማር ተልዕኮዋቸው ተስተጓጉለው ከርመዋል” ሲሉ ወቅታዊ ሁኔታውን በአሃዝ አስደግፈው ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ በክልሉ በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ “እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው” እና “ጉስቁልና ካረፈባቸው” ዘርፎች መካከል የትምህርት ዘርፉ አንዱ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ያለው የክልሉ የትምህርት ዘርፍ የዕድገት ምጣኔ፤ “ከዜሮ በታች እንደሆነ ይገመታል” ሲሉም ተደምጠዋል።  

“ለአብነት በ2016 በጀት ዓመት ብንመለከት፤ ዕድገቱ ኔጌቲቭ ስድስት በመቶ በመሆኑ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ በመሆኑ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን እናየዋለን። የዚህ አሉታዊ ዕድገት ምጣኔ መነሻው፤ በክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በተከታታይ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አለመቻላቸው ነው” ሲሉ አቶ አረጋ ዝቅተኛ ምጣኔ የተመዘገበበትን ምክንያት አስረድተዋል።

“በ2016 በጀት ዓመት ብንመለከት፤ ዕድገቱ ኔጌቲቭ ስድስት በመቶ በመሆኑ [የትምህርት] ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ በመሆኑ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን እናየዋለን”

– አቶ አረጋ ከበደ፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

በትምህርት ዘርፉ ያለውን ችግር “የትውልድ ቅብብሎሽን የሚገታ ታላቅ ስብራት” በማለት የጠሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  የአማራ ክልል ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ “በጉልህ መክሮ አቅጣጫ ሊያስቀምጥበት ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል። አፈ ጉባኤ ፋንቱም በትላንቱ የመክፈቻ ንግግራቸው፤ የምክር ቤቱ አባላት ለጉዳዩ “ተገቢውን ትኩረት” እንዲሰጡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)