የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት የመጀመሪያው ዙር ቴክኒካዊ ድርድር ተጠናቀቀ። በቱርክ አንካራ ከተማ በተካሄደው ድርድር፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ሞሐመድ ዑመር ተገኝተዋል።
በቱርክ በኩል በድርድሩ የተገኙት፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በታህሳስ ወር መጀመሪያ ፊት ለፊት ከመገናኘታቸው በፊት በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ ተመላልሰው ውይይቱን ያመቻቹት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ናቸው። በዛሬው ድርድር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የሁለቱን ሀገራት ልዑካን ቡድን በተናጠል እና በጋራ ማነጋገራቸውን መስሪያ ቤታቸው አስታውቋል።
ሐካን ፊደን በተናጠል እና በጋራ በተደረጉት ውይይቶች፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነት በበረታበት ዓለም ውስጥ ቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በአጽንኦት መናገራቸውን የቱርክ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አመልክቷል። ፊዳን በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተጀመረው ድርድር “የአፍሪካን ቀንድ መጻኢ ጊዜ ታሪካዊ ዕድል ይወክላል” በማለት ፋይዳውን ገልጸዋል።

በዛሬው የመጀመሪያ ዙር “ቴክኒካዊ ድርድር”፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንካራ ቃል ኪዳን “ዋነኛ ዓላማ እና መንፈስ ያላቸውን ቁርጠኝነት” ማሳየታቸውን የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል። ልዑካኑ የአንካራ ቃል ኪዳንን ራዕይ እውን እንዲሆን ለማድረግ እና ለሁለቱ ሀገራት ጠቃሚ ለሆነ ዘላቂ ልማት መሰረት ለመጣል፤ “ተጨባጭ ስራ ማከናወን እንደጀመሩም” በመግለጫው ሰፍሯል።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የመጀመሪያው ዙር “ቴክኒካዊ ድርድር” ያስገኘው ውጤት በይፋ ባይገለጽም፤ ሁለቱ ሀገራት በተመሳሳይ መልኩ በቱርክ አመቻችነት የሚያደርጉት ቀጣይ ድርድር በመጪው መጋቢት ወር ለመቀጠል መስማማታቸው ይፋ ተደርጓል። ቱርክ በፕሬዝዳንቷ አማካኝነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለማሸማገል ያደረገችው ጥረት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተካርሮ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ማርገብ ችሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር )