የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በሁለት ክሶች ጥፋተኛ ተባሉ 

በቤርሳቤህ ገብረ

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረቡባቸው ሁለት ክሶች ጥፋተኛ ተባሉ። ፍርድ ቤቱ ትላንት ረቡዕ የካቲት 26፤ 2017 በዋለው ችሎት፤ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች አራት ተከሳሾች ላይም የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ያስተላለፈው የጥፋተኝነት ውሳኔ፤ “ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል”፣ “የመንግስትን ስራ በማያመች ሁኔታ በመምራት”፣ “የማይገባ ጥቅም በማግኘት ጉቦ በማቀባበል” እና “የሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት” የሙስና ወንጀል ነው። የሲዳማ ክልል ዐቃቤ ህግ፤ የቀድሞውን ከንቲባ ጨምሮ በአራት ተከሳሾች ላይ ክስ የመሰረተው ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ነበር። 

ከአቶ ጸጋዬ ጋር በአንድ መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ የቀድሞው ከንቲባ ሚስት አባት የሆኑት አቶ ተሰማ ዳንጉሼ ይገኙበታል። የሀዋሳ ከተማ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ ታሪኩ ታመነ ሌላኛው ተከሳሽ ሲሆኑ፤ እርሳቸው በሚመሩት ቢሮ ውስጥ መሀንዲሶች የነበሩት አቶ ታፈሰ ቱናሻ እና አቶ ሰይፉ ደሌሳም በዚሁ የክስ መዝገብ ስር ተካትተዋል።  

የቀድሞው የቢሮ ምክትል ኃላፊ እና ሁለቱ መሀንዲሶች ላይ የክልሉ ዐቃቤ ህግ ክስ ያቀረበው፤ በከተማ ተቋማዊነት እና መሰረተ ልማት ፕሮግራም (urban institutional and infrastructure development program) ስር ሲከናወኑ ከቆዩ አራት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ነው። በዚህ ፕሮጀክት ስር ከሚሰሩ ፕሮጀክቶች አንዱ የሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ነው። 

ሶስቱ ተከሳሾች በዚህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 2.2 ሚሊዮን ብር ገደማ “ያለ አግባብ ክፍያ እንዲፈጸም” እና “እንዲመዘበር” አድርገዋል በሚል ነው የተወነጀሉት። በከተማ ተቋማዊነት እና መሰረተ ልማት ፕሮግራም ስር የሚተገበረው የሀዋሳ ታቦር ተራራ ልማት ፕሮጀክትም 1.46 ሚሊዮን ብር “ያልተገባ ክፍያ” እንደተፈጸመበት ዐቃቤ ህግ በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።

ከሀዋሳ ከተማ ሚሊኒየም ፓርክ (gateway) ፕሮጀክት ስራ ጋር በተገናኘ፤ ተከሳሾቹ በተመሳሳይ 1.03 ሚሊዮን ብር ገደማ “ያለአግባብ እንዲመዘበር” ማድረጋቸውን ዐቃቤ ህግ በክሱ አትቷል። ተከሳሾቹ በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ከተሰሩ ሁለት የእግረኛ መንገዶች ጋር በተያያዘ ፈጽመውታል የተባለው የወንጀል ድርጊትም በክሱ ላይ ተካትቷል። 

የመጀመሪያው የእግረኛ መንገድ መነሻ ኬራዊ ሆቴል ሲሆን መድረሻው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፉራ ቅርንጫፍ ድረስ ነው። ሁለተኛው የእግረኛ መንገድ ከሳውዝ ስታር ሆቴል ተነስቶ እስከ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳካ ቅርንጫፍ ድረስ ያለውን ቦታ የሚሸፍን ነው። 

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና ሁለቱ መሀንዲሶች፤ በእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች 93 ሚሊዮን ብር ያህል “ከመመሪያ እና ደንብ ውጭ” የግዢ ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ተከስሰዋል። ሶስቱ ተከሳሾች በቀረበባቸው “የህዝብ እና በመንግስት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ” እና “የመንግስት ስራ በማይመች አኳኋን በመምራት” የሙስና ወንጀል ክስ፤ በትላንቱ የችሎት ውሎ ጥፋተኛ መባላቸውን የሲዳማ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል። 

በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ የተፈጸሙት የወንጀል ድርጊቶች፤ አቶ ጸጋዬ ቱኬ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ እንደሆነ የክልሉ ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ አመልክቷል። በፕሮጀክቶቹ የግዢ መመሪያ አሰራር ስርዓትን በበላይነት የሚመሩት አቶ ጸጋዬ መሆናቸውንም ዐቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ አስታውሷል። 

አቶ ጸጋዬ ለፕሮጀክቶቹ የተፈጸሙ ግዢዎችን “በማንዋል መሰረት ማድረግ” ሲገባቸው፤ “ይሄንን ወደ ጎን በመተው” “በህገ ወጥ አግባብ መርተዋል” በሚል ተወንጅለዋል። ይህንን በመንተራስም የክልሉ ዐቃቤ ህግ “የህዝብ እና የመንግስት ሀብት ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ” እና “ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል” በአቶ ጸጋዬ ላይ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር። 

በዚህ ክስ ቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በፍርድ ቤት “ጥፋተኛ” መባላቸውን የሲዳማ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ጸጋዬ በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉበት ሌላው ጉዳይ፤ በመንግስት የመኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው እያለ ከስልጣን እስከተነሱበት ጊዜ ድረስ “የቤት ኪራይ ገንዘብ ይቀበሉ ነበር” የሚለው ነው። 

የቀድሞው ከንቲባ ለቤት ኪራይ በወር 10 ሺህ ብር በድምሩ 260 ሺህ ብር “ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል” በሚል በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ የመረመረው ፍርድ ቤቱ፤ አቶ ጸጋዬን “ጥፋተኛ ናቸው” ማለቱን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ምንጮች ገልጸዋል። የሀዋሳ ከተማ ፍርድ ቤት በትላንቱ ውሎው፤ አቶ ጸጋዬ ላይ ከቀረቡ ሶስት ክሶች በአንደኛው “ነጻ መሆናቸውን” ውሳኔ ማስተላለፉንም እነኚሁ ምንጮች አስረድተዋል።

ሶስተኛው የአቶ ጸጋዬ ክስ “እምነት አጉድለዋል” በሚል የቀረበባቸው ቢሆንም፤ “ዐቃቤ ህግ ክሱን በሚገባ አላስረዳም” በሚል ፍርድ ቤቱ ከክሱ ነጻ አድርጓቸዋል። ዐቃቤ ህግ የእምነት ማጉደል ክስ ያቀረበው፤ ተከሳሹ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በመንግስት እንዲገለገሉበት የተሰጣቸው 488 ሺህ ብር የሚያወጡ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች፤ “ቤቱን ለቅቀው ሲወጡ አልተገኙም” በሚል ነበር።

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ቀርቦባቸው ከነበሩ ሁለት ሌሎች ክሶች በተመሳሳይ ሁኔታ “ነጻ ናቸው” መባላቸው ይታወሳል። ፍርድ ቤቱ ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረው ችሎት አቶ ጸጋዬ ከቀረቡባቸው ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ ቢወስንም፤ በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታዩ ባሉት ሌሎች ክሶቻቸው ምክንያት ከእስር ሳይለቀቁ መቅረታቸው ይታወሳል።  

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትላንትናው የችሎት ውሎው፤ የቀድሞው ከንቲባ ሚስት አባት የሆኑት አቶ ተሰማ ዳንጉሼ ላይ የጥፋተኛነት ውሳኔ ማስተላለፉን የሲዳማ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል። አቶ ተሰማ የተከሰሱት፤ ጉዳይ እንዲፈጻምላቸው ከሚፈልጉ 11 የተለያዩ ማህበራት 150 ሺህ ብር በመሰብሰብ “እኔ አስፈጽምላቸዋለሁ” በማለት ጉቦ በማቀባበል “የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” በሚል ነበር።

በትላንቱ የችሎት ውሎ፤ የሀዋሳ ከተማ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ ታሪኩ በቀረበባቸው ሁለተኛ ክስ ጥፋተኛ ተብለዋል። አቶ ታሪኩ ጥፋተኛ የተባሉት፤ በሀዋሳ ከተማ ለሁለት የመሬት ይዞታዎች ሀሰተኛ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ክስ ነው። 

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በአቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ እንዲሁም በተከሳሾቹ የሚቀርብ የቅጣት ማቅለያን ለመስማት ለሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ መጋቢት 3፤ 2017 ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል። የፍርድ ቤቱ የትላንት ችሎት ውሎ፤ በጥብቅ የጸጥታ ጥበቃ ስር የተካሄደ እንደነበር በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)