የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በመንፈቅ ዓመት ውስጥ ከ6.4 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ መሰብሰቡን ገለጸ 

በቤርሳቤህ ገብረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ6.4 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ መሰብሰቡን አስታወቀ። ቢሮው ያለባቸውን “ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ ለመክፈል ፈቃደኛ አልሆኑም” ያላቸውን 62 ግለሰቦች ሀገር እንዳይወጡ ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ስም ዝርዝራቸውን ማስተላለፉን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ያቀደው ጠቅላላ የገቢ መጠን 230 ቢሊዮን ብር ነው። የከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከታክስ ገቢዎች ለማግኘት ያቀደው 150.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ እስከ መንፈቅ ዓመት 111.5 ቢሊዮን ብር ማግኘት መቻሉን ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ይፋ ተደርጓል።  

የከተማይቱ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ከሰባት ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ዓመታዊ ገቢ 30 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ እድገት የተመዘገበው “የታክስ ምጣኔ ሳይቀይር” እንደሆነም በወቅቱ አጽንኦት ሰጥተው ነበር።

የከተማይቱ አስተዳደር “የታክስ መሰረትን በማስፋት” እንዲሁም “ብክነት እና ብልሹ አሰራርን በመከላከል” የገቢ መጠኑን ማሳደግ መቻሉን በወቅቱ አብራርተዋል። ከንቲባዋ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት፤ ለግብር ስረዛ የቀረቡ ዶክመንቶች ላይ ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገ ፍተሻ “10 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን” ነው።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 27፤ 2017 በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ፤ ባለፈው መንፈቅ ዓመት ውስጥ ከ6.4 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ መሰብሰቡን ገልጿል። ቢሮው “የግብር ዕዳቸውን ሳይወጡ የሚሰወሩ” ያላቸውን ግብር ከፋዮች “በአግባቡ ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል”፤ የዕዳ ክትትል እና አስተዳደር የስራ ክፍል በአዲስ መልክ ማደራጀቱን በዚሁ መግለጫው ላይ አንስቷል። 

ቢሮው ይህንን የስራ ክፍል በአዲስ መልክ ለማደራጀት የተገደደው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የታክስ ዕዳ “ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ” ቢሮው ገልጾ ነበር። የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አዲስ አደረጃጀት እና አሰራር ካለፈው ጥቅምት ወር ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው፤ በከተማይቱ “የታክስ ዕዳ ከአመት አመት እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ” በወቅቱ አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ 20 ቢሊዮን ብር ያህል ያልተሰበሰበ የታክስ ዕዳ እንዳለ የከተማይቱ የገቢዎች ቢሮ ባለፈው ጥቅምት ወር አስታውቆ ነበር። በከተማይቱ ገቢዎች ቢሮ ስር ያለው የዕዳ ክትትል እና አስተዳደር የስራ ክፍል፤ ያልተከፈለ እና ያልተሰበሰበ እዳን ከመለየት ጀምሮ እስከ መሸጥ ስልጣን ያለው ነው።

የገቢዎች ቢሮው በዛሬው ዕለት ባወጣው መረጃ፤ “ለከተማይቱ ሁለንተናዊ ልማት ሊውል ይገባ” ነበር ያለው ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር በ62 ግለሰቦች ላይ በዕዳነት ተመዝግቧል። እነዚህ ግለሰቦች ያለባቸውን ዕዳ እንዲከፍሉ “ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም”፤ ክፍያቸውን ለመፈጸም “ፈቃደኛ አለመሆናቸውን” ቢሮው በዚሁ መረጃው ላይ አመልክቷል። 

በዚህ መሰረት ቢሮ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት፤ ግለሰቦቹ ከሀገር እንዳይወጡ ለፌደራል ኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ስም ዝርዝራቸውን ማስተላለፉን ገልጿል። የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አንድ ታክስ ከፋይ የሚጠበቁበትን ክፍያዎች ሳይከፍል “ከሀገር ሊወጣ ይችላል” የሚል በቂ ምክንያት” ካለው፤ “ከሀገር መውጣትን ለመከልከል የሚያስችል ትዕዛዝን” ተፈጻሚ ሊያደርግ እንደሚችል በ2008 ዓ.ም በወጣው “የፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ” ላይ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)