የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በፌደራል ፍርድ ቤት ከቀረቡባቸው ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ ተፈረደላቸው

🔴 አቶ ጸጋዬ ቱኬ በሌላ ፍርድ ቤት ክሶች ያለባቸው በመሆኑ በእስር ላይ ይቆያሉ ተብሏል

በተስፋለም ወልደየስ

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ በዛሬው ዕለት የፍርድ ውሳኔ እንደተሰጣቸው ከተከላካይ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ገብረመድህን ተክላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከቀድሞው ከንቲባ ጋር በአንድ መዝገብ የተከሰሱት የሲዳማ ክልል የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበራ አሬራ እና የአቶ ጸጋዬ የእህት ልጅ የሆኑት አቶ አብርሃም አመሎም በተመሳሳይ በነጻ መሰናበታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል። 

በሶስቱ ተከሳሾች ላይ የፍርድ ውሳኔውን የሰጠው፤ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ነው። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 11፤ 2017 በዋለው ችሎት፤ “ሶስቱም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ሁለቱንም የወንጀል ክሶች ያልፈጸሙና በሚገባ የተከላከሉ መሆናቸው በነጻ ተሰናብተዋል” ሲል ውሳኔ ማስተላለፉን ጠበቃ ገብረመድህን ገልጸዋል። 

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ በአቶ ጸጋዬ እና በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ክስ የመሰረተው፤ “የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” እንዲሁም “በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስለው አቅርበዋል” በሚል ነበር። ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል፤ ሶስቱም ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ገደማ ብይን ሰጥቷል።

ይህን ተከትሎ የተከላካይ ጠበቆች፤ ተከሳሾቹን ጨምሮ ስድስት የሰው ምስክሮችን እና 12 የተለያዩ አይነት የሰነድ አይነቶችን ማቅረባቸውን አቶ ገብረመድህን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የክልሉ ዐቃቤ ህግ እና ተከላካይ ጠበቆች ያቀረቧቸውን ምስክሮች እና ሰነዶች የመረመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል፤ ፍርድ ለመስጠት ለሁለት ጊዜያት ያህል ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ በዛሬው ዕለት ውሳኔውን አስተላልፏል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባን በነጻ ቢያሰናብትም፤ አቶ ጸጋዬ በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡባቸው ሌሎች ክሶች ስላሉ ከእስር እንደማይለቀቁ አቶ ገብረመድህን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ባለው መዝገብ፤ አቶ ጸጋዬን ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች “በህገ ወጥ መንገድ ሰነድ ማዘጋጀት፣ ጉቦ መቀባበል እና ስልጣንን አላግባብ መጠቀም” የሚሉትን ጨምሮ አምስት ክሶች ቀርበውባቸው ነበር። 

የከተማይቱ ፍርድ ቤት ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ባስቻልከው ችሎት፤ “በዐቃቤ ህግ ማስረጃ አልተረጋገጠም” በሚል ከአምስቱ ክሶች አንዱን ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም። አቶ ጸጋዬ በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡባቸውን አራት ክሶች እንዲከላከሉ በተሰጣቸው ብይን መሰረት፤ ይህንኑ ሂደት ማጠናቀቃቸውን ጠበቆቻቸው ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ በቀረቡት ክሶች ላይ በዚህ ወር መጨረሻ ገደማ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል። 

አቶ ጸጋዬ ከእስር ለመለቀቅ የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን ቢጠብቁም፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት “በነጻ የተሰናበቱት” የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር ግን ከሰዓት በኋላ ከእስር ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ገብረመድህን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ከሁለቱ ተከሳሾች ጋር በአንድ መዝገብ የተካተቱት አቶ አብርሃም አመሎ፤ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው ሲከራከሩ የቆዩ ናቸው።

ሀዋሳ ከተማን ለሶስት ዓመታት የመሩት አቶ ጸጋዬ፤ በብልሹ አሰራር እና የአፈጻጸም ድክመት ተገምግመው ከኃላፊነታቸው የተነሱት በነሐሴ 2015 ዓ.ም ነበር። በዚሁ ወቅት በተካሄደው ግምገማ አቶ ጸጋዬ “በህግ እንዲጠየቁ ውሳኔ ተላልፎባቸው” የነበረ ቢሆንም፤ ውሳኔው ለሁለት ወራት ያህል ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።

የቀድሞው ከንቲባ በጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በጥቅምት 2016 ዓ.ም. ከአሜሪካ ሲመለሱ በቦሌ አየር ማረፊያ እንደነበር ይታወሳል። የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ፤ በአቶ ጸጋዬ ላይ የመጀመሪያውን የክስ መዝገብ የከፈተው በጥር 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)