ኢትዮጵያ በሩብ ዓመት ውስጥ ብቻ ከጥይት ሽያጭ 30 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ማግኘቷን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ   

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ለውጭ ሀገራት ከሸጠቻቸው ጥይቶች፤ “ከ30 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ” ገቢ ማግኘቷን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ሀገሪቱ ለውጭ ሀገር ገበያ የሚቀርቡ ክላሽ፣ ስናይፐር፣ ብሬን፣ ዲሽቃ፣ ታንክ እና ሁሉንም አይነት መድፎች “የማምረት አቅም ያለው” ፋብሪካ መገንባቷንም አብይ አስታውቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ያሉት፤ በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በቶኬ ኩታዬ ወረዳ የሚገኘውን የሆሚቾ ጥይት ፋብሪካ ትላንት ረቡዕ የካቲት 26፤ 2017 በጎበኙበት ወቅት ነው። አብይ በዚሁ ወቅት በሰጡት ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ “በተወሰነ ደረጃ” ጥይት እና መሳሪያ “የማምረት ሙከራዎች” እንደነበሩ አስታውሰዋል። 

በ2015 ዓ.ም በአምቦ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተከላው የተጀመረው ዘመናዊ ፋብሪካ፤ “ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ” ጥይቶችን እና የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎችን ወደ ማምረት መሸጋገሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ይፋ አድርገዋል። ፋብሪካው “የሮቦቲክስ” ቴክኖሎጂን በመጠቀም፤ “በሰዓት በጣም ከፍተኛ የማምረት አቅም ያለው” መሆኑንም አመልክተዋል። 

ይህ ፋብሪካ “ለገበያ በቂ የሆኑ”፤ “ክላሽ” እና “ስናይፐር” ጠብመጃዎችን እንዲሁም “ብሬን” እና “ዲሽቃ” የተሰኙ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የሚያመርት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ፋብሪካው “ታንክ” እና “ሁሉንም አይነት መድፎች” የማምረት አቅም ያለው መሆኑን አብይ ገልጸዋል። 

ፋብሪካው ያመረታቸው ጥይቶች ባለፉት ሶስት ወራት ለውጭ ሀገራት ተሽጠው “ከ30 ሚሊዮን ያላነሰ ዶላር” ገቢ መገኘቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል። አዲሱ ፋብሪካ የጥይት ምርቶቹን ለመሸጥ “ከበርካታ ሀገራት” ጋር የኮንትራት ውል መፈጸሙንም አክለዋል።

በ2014 ዓ.ም “ጥይት እንገዛ ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “እነዚህን አይነት ነገሮች ከመግዛት ወጥተን፣ አምርተን፣ ለሌሎች የምንሸጥ ሀገር መሆናችን እና በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄ አቅም ተገንብቶ በማየቴ በጣም ከፍተኛ ክብር እና ደስታ ይሰማኛል” ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተዋል። “ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት አቅም ሲኖራት ደስ ይላል” ያሉት አብይ፤ የፋብሪካው የማምረት አቅም ሀገሪቱን “የሚመጥን” እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ኢትዮጵያ የፋብሪካው አይነት “ስትራቴጂክ አቅሞች” ካልገነባች፤ “በሆነ ጊዜ ማንም መጥቶ በቀላሉ ጥቃት ሊፈጽምባት ይችላል” የሚል ግምገማ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መለስ ብለው አስታውሰዋል። “አሁን ማምረት፣ መሸጥ ስለቻልን፤ ኢትዮጵያን የማጽናት፣ ኢትዮጵያን የማስቀጠል፣ ለልጆቻችን፣ ባመረ እና በተሻለ ደረጃ የማስረከቡ ነገር፤ በጣም መስመር እየያዘ፣ በሁሉም መስክ እመርታዎቹ እየታዩ፣ እየተጨበጡ መጥተዋል” ሲሉም ተደምጠዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ለወታደር የሚሆን ልብስ እና ጫማ ከውጭ ሀገር ያስመጣ እንደነበር የጠቀሱት አብይ፤ በአሁኑ ወቅት እነዚህን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን አስገንዘበዋል። የመከላከያ ሰራዊት በአሁኑ ጊዜ ለወታደሮች ጫማ አምርቶ፤ “የሚያንሰውን ከሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች” እንደሚቀበልም አብራርተዋል። 

“እኔ ወታደር ነኝ። በውትድርና አካባቢ የሚጎድሉ ነገሮች፤ በኦፕሬሽን ጊዜ እንዴት አስቸጋሪ እንደሆኑ እረዳለሁ። ይገባኛል። አሁን ኢትዮጵያ ስጋት የለባትም። ጭንቅላት ያላቸው ልጆች አሏት። ጀግና ወታደሮች አሏት። ከግብዓት አንጻር የነበረባትን ውስንነት ከሞላ ጎደል ፈትታለች” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። 

የኢትዮጵያ መንግስት በዘንድሮው ዓመት “ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው” ሴክተሮች አንዱ ኢንዱስትሪ መሆኑን የጠቆሙት አብይ፤ ዘርፉ እስከ 12 ፐርሰንት እድገት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል። ከዚህ አኳያ በመከላከያ ኢንዱስትሪ ብቻ የመጣው እድገት “በጣም ተስፋ ሰጪ” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈገግታ ታጅበው አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንትናው ዕለት የጎበኙት አዲሱ የጥይት ፋብሪካ፤ በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ስር የሚገኝ ነው። ፋብሪካው የሚገኝበት የሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፤ በደርግ ዘመነ መንግስት የተገነባ ነው። 

በ1979 ዓ.ም. የተመሰረተው የሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች የተገነቡት፤ በሶቪየት ህብረት እና በሰሜን ኮሪያ እርዳታ እንደሆነ በጦር መሳሪያዎች እና ወታደራዊ ቁሳቁሶች ላይ ጥናት ከሚያደርግ እና የማማከር አገልግሎት ከሚሰጥ የአውስትራሊያ ድርጅት የተገኘ መረጃ ያሳያል። ሆሚቾ ሲመሰረት የነበረው ስያሜ “ፕሮጀክት 130” የተሰኘ እንደነበር በዚሁ መረጃ ላይ ተጠቅሷል። 

የመከላከያ ሚኒስቴር ስር የነበረው ሆሚቾ ኢንዱስትሪ፤ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ለዘጠኝ ዓመታት በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ስር ሲተዳደር ቆይቷል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በሜቴክ ላይ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ተከትሎ፤ ኮርፖሬሽኑ ሆሚቾ እና ሌሎች ሶስት ወታደራዊ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር እንዲያስረክብ ተደርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)