በቤርሳቤህ ገብረ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፤ በጥቅሉ 18 ሄክታር ስፋት ያላቸውን 427 ቦታዎች ለሊዝ ጨረታ ሊያቀርብ ነው። በመዲናይቱ ዘጠኝ ክፍለ ከተሞች የሚገኙት እነዚህ ቦታዎች፤ ለመኖሪያ እና ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸው ተገልጿል።
በከተማይቱ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የመሬት ዝግጅት እና ባንክ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ለጨረታ የሚቀርቡት ቦታዎች “በተለያየ አግባብ ወደ መሬት ባንክ የገቡ ይዞታዎች” ናቸው። በአሁኑ ዙር ጨረታ በቦሌ እና ልደታ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የመሬት ይዞታዎች እንዳልተካተቱ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ለጨረታ የሚቀርቡት ቦታዎች ዝርዝር፤ በነገው ዕለት ታትሞ በሚወጣው “አዲስ ልሳን” ጋዜጣ ማግኘት እንደሚቻል የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ይህንን ተከትሎ የጨረታ ሰነድ ሽያጩ “ከእጅ ንኪኪ በጸዳ መልኩ” ከመጪው ሰኞ መጋቢት 1 እስከ መጋቢት 12 ድረስ ባሉት ቀናቶች የሚከናወን መሆኑንም ጠቁሟል።

የጨረታ ሰነዱ ሽያጭ የሚከናወነው “ቱ መርካቶ” እና “አዲስ ላንድ አፍሮ ቴንደር” በተሰኙ ሁለት ድረ ገጾች አማካኝነት ነው። የሊዝ ጨረታው ከመጋቢት 15 ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ የስራ ቀናት፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚካሄድ መሆኑን ቢሮው አመልክቷል።
ይህ ጨረታ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቋርጦት የነበረውን የሊዝ ጨረታ በድጋሚ ከጀመረ በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ የሚከናወን ይሆናል። የከተማይቱ አስተዳደር በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ ሁለት የመሬት የሊዝ ጨረታዎችን አካሄዷል።
ከአምስት ወር በፊት የተካሄደው ጨረታ፤ በአስር ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 285 ቦታዎች ለተጫራቾች የቀረቡበት ነው። በዚህ ዙር ጨረታ የተሰጠው ዝቅተኛ ዋጋ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለሚገኝ ይዞታ ሲሆን የገንዘብ መጠኑ በካሬ 12,320 ብር ነበር። በጨረታው ከፍተኛ የሆነው በካሬ 306,600 ብር የገንዘብ መጠን የተመዘገበው፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለሚገኝ እንደነበር ቢሮው በወቅቱ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት ከመሬት ሊዝ ለመሰብሰብ ያቀደው 40.09 ቢሊዮን ብር ነው። አስተዳደሩ የመሬት ሊዝ ጨረታን መልሶ በጀመረበት በግንቦት 2015 ዓ.ም.፤ ከተመሳሳይ የገቢ ምንጭ ለማግኘት አቅዶ የነበረው የገንዘብ መጠን 12.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል።
የከተማ አስተዳደሩ በመጪዎቹ ጊዜያት የመሬት ሊዝ ጨረታ ማውጣት እንደሚቀጥል የመሬት ዝግጅት እና ባንክ ጥበቃ ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። በመዲናይቱ የከተማ ቦታ በሊዝ የሚያዘው፤ በጨረታ ወይም በምደባ ስልት እንደሆነ በአዋጅ ተደንግጓል።
የከተማ ቦታን በሊዝ መያዝን በተመለከተ በ2011 ዓ.ም. የጸደቀው አዋጅ፤ የከተማ ቦታን የመጠቀም መብት በሊዝ የሚፈቀደው “ለህዝቡ የጋራ ጥቅምና ዕድገት እንዲውል ለማድረግ” እንደሆነ ያትታል። አንድ ከተማ ፕላን ያለው ከሆነ፤ በሊዝ እንዲያዝ የሚፈቀደው መሬት “የኘላኑን የቦታ አጠቃቀም ድንጋጌ” መከተል እንደሚገባውም በዚሁ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)