በትግራይ ክልል “ከመንግስት እውቅና ውጪ” የሚደረግ የሰራዊት እንቅስቃሴ “በአስቸኳይ እንዲቆም” የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትዕዛዝ ሰጡ። ይህን ትዕዛዝ ቸል በሚሉ አካላት ላይ “አስቸኳይ” “የእርምት እርምጃ” እንዲወሰድም አሳስበዋል።
አቶ ጌታቸው ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላም እና ጸጥታ ካቤኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ለሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በጻፉት ደብዳቤ ነው። ከሁለት ቀናት በፊት የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፤ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር በሚተዳደረው “ድምጺ ወያነ” ቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል ይፋ የተደረገው በዛሬው ዕለት ነው።
“ህገወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ስለማሳሰብ” በሚል ርዕስ ስር የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፤ “ህገ ወጥ ጉባኤ ያደረገው” በሚል የሚጠራውን ቡድን “ስልጣን ለማግኘት እንቅስቃሴ” እያደረገ እንደሆነ ይወነጅላል። አቶ ጌታቸው የቡድኑን ማንነት በደብዳቤያቸው በግልጽ ባያስቀምጡም፤ ከዚህ ቀደም ባወጧቸው መግለጫዎች በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራ ስብስብ የህወሓትን “ህገ ወጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጓል” በማለት ሲተቹ ቆይተዋል።
ይህ ቡድን “የሰራዊት አመራሮች ውሳኔ” በሚል ጀምሮታል ያሉትን “ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዲያቆም” የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መወሰኑን አቶ ጌታቸው በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ባወጣው መግለጫ፤ “ከኮር በላይ የሆኑ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች” ባደረጉት ስብሰባ ላይ ያሳለፉትን ውሳኔ “መሰረታዊ ስህተቶች ያለባቸው” እና “ተፈጻሚነት የሌላቸው መሆናቸውን” አስታውቆ ነበር።
አቶ ጌታቸው ባለፈው ረቡዕ በጻፉት ደብዳቤ፤ የሰራዊት አመራርም ይሁን ወይም ሌላ አካል “አለኝ” የሚለውን እምነት “ስርዓት በጠበቀ መንገድ” ማቅረብ የሚችልበት አግባብ እንዳለ ጠቅሰዋል። ይህ ባለበት ሁኔታ “የሰራዊቱን አሃዶች በየጣቢያው እና ወረዳው በማሰማራት ስርዓት ለማፍረስ” የሚደረገው አካሄድ፤ “ህዝብን ወደ ግጭትን እንዲገባ የሚያደርግ ነው” ብለዋል።
ይህ ሁኔታ የትግራይን የጸጥታ ኃይል “የሚያከስር” እና “ስርአት አልባነትን የሚያመጣ አካሄድ” እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹንም አቶ ጌታቸው በደብዳቤያቸው አንስተዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት፤ ለትግራይ ህዝብ “ትልቅ ተቋም እንዲሆን የተቋቋመ” ያሉት ሰራዊት “እስካሁን የሚገባውን ትኩረት አለማግኘቱን” በደብዳቤያቸው አንስተዋል።

በዚህ ምክንያት የሚፈጠር ችግር ቢኖርም እንኳ፤ ሰራዊቱ እርሳቸው “ማህተም መንጠቅ” ሲሉ በጠሩት ተግባር ላይ ሊሰማራ እንደማይገባ አስገንዝበዋል። ሰራዊቱ በዚህ ተግባር “ተዘፍቋል” ሲሉ የወነጀሉት አቶ ጌታቸው፤ ይህ ሁኔታ “በትግራይ የማያባራ ግጭት ከመፍጠሩ” በተጨማሪ “ለውጭ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርግ” እንደሆነ አሳስበዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲህ አይነት ድርጊቶች ከዚህ ቀደም ተፈጽመውባቸዋል በሚል በደብዳቤያቸው የጠቀሱት፤ የሰሜን ምዕራብ እና የማዕከላዊ ዞኖችን ነው። በሰራዊቱ የግንባር መሪዎች የሚመራ ተመሳሳይ “አዋኪ እንቅስቃሴዎች” በደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ እና ምስራቅ ዞኖች እንዲሁም በመቐለ ከተማ ለመተግበር ዝግጅቶችን ማገባደዳቸውን ለማወቅ እንደተቻለም አቶ ጌታቸው አመልክተዋል።
“ይህ አደገኛ አካሄድ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምስራቅ ባሉ ሁሉም ግንባሮች “ከመንግስት እውቅና ውጪ የሚደረግ” የሰራዊት እንቅስቃሴ እንዳይኖር አሳስበዋል። አቶ ጌታቸው “ህገወጥ” እና “አፍራሽ” ሲሉ የጠሩትን የሰራዊት እንቅስቃሴ እንዲያስቆሙ ትዕዛዝ የሰጡት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትላቸው ለሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ነው።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የሰጡትን ትዕዛዝ ለመፈጸም ቸል በሚሉ አካላት ላይ ሌተናል ጄነራል ታደሰ “አስቸኳይ” “የእርምት እርምጃ” እንዲወስዱም አሳስበዋል። አቶ ጌታቸው ይህን ትዕዛዝ ቢሰጡም፤ በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ጎራ የትግራይ ሰራዊት አዛዦች ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ባካሄዱት ስብሰባ ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)