በትግራይ ክልል “በአንዳንድ ቴክኒካዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ተቋርጦ” ነበር የተባለው የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በማሰልጠን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ሂደት፤ “በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንደገና እንደሚጀምር” የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ። ሂደቱ ዳግም የሚጀመረው፤ በመቐለ እና በዕዳጋ ሀሙስ በሚገኙ ማዕከላት ነው።
የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ህይወት የመመለስ ሂደት እንደገና እንደሚጀመር የተገለጸው፤ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ መኩሪያው ዛሬ በመቐለ ከተማ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰላም እና ጸጥታ ካቤኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ የሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ፤ ለሂደቱ መሳካት ክልሉ “አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር” እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ባለፈው ህዳር ወር ተጀምሮ የነበረው ይህ ሂደት፤ “የቀድሞ ተዋጊዎችን የማረጋገጥ፣ ዲሞቢላይዝ የማድረግ፣ የመመዝገብ እና የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል” ስራዎችን ያካትታል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፤ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ከ174 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገልጿል። ከእነዚህ የቀድሞ ተዋጊዎች ውስጥ ስምንት ሺህ የሚሆኑት በትግራይ ክልል የሚገኙ ናቸው።
የመከላከያ ሰራዊትን በመወከል ሂደቱን የሚያስተባብሩት ብርጋዴየር ጄነራል ደርቤ፤ በትግራይ ክልል በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ 67 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን በፕሮግራሙ በማሳተፍ ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል መታቀዱን ይፋ አድርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)