ኢትዮጵያ የመከላከያ አቅሟን የምታጎለብተው “ትናንሽ አቅም ይዘው ለሚሳሳቱ ኃይሎች ብዙ ጊዜ [ሰጥተው] እንዲያስቡ ለማስቻል” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እነዚህን አቅሞች የምናጎለብተው ለመዋጋት አይደለም። ውጊያን ለማስቀረት ነው” ብለዋል።
አብይ ይህን ያሉት “ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ” የተባለ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ማምረቻ ትላንት ቅዳሜ የካቲት 29፤ 2017 በመረቁበት ወቅት በሰጡት ገለጻ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ተገኝተው ማብራሪያ ሲሰጡ፤ የትላንቱ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ባለፈው ረቡዕ በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የሆሚቾ ጥይት ፋብሪካ የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ኢትዮጵያ ከወታደራዊ ግብዓት አንጻር የነበረባትን “ውስንነት ከሞላ ጎደል ፈትታለች” ብለው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት፤ ሀገሪቱ ጥይት ከመግዛት ወጥታ፣ በሆሚቾ ፋብሪካ አምርታ፣ ለሌሎች ሀገራት የምትሸጥ መሆኗን ነው።

በሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተገነባው ፋብሪካ፤ ለውጭ ሀገር ገበያ የሚቀርቡ ክላሽ፣ ስናይፐር፣ ብሬን፣ ዲሽቃ፣ ታንክ እና ሁሉንም አይነት መድፎች “የማምረት አቅም ያለው” መሆኑንም አብይ በወቅቱ ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋብሪካ ጉብኝትም ሆነ ያቀረቡት ገለጻ፤ ኢትዮጵያ “ከኤርትራ ጋር ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ለመግባት በዝግጅት ላይ ለመሆኗ ማሳያ” አድርገው የቆጠሩ ወገኖች አሉ።
ይህን አመለካከት የተረዱ የሚመስሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንቱ ገለጻቸው፤ “እነዚህን አቅሞች የምናጎለብተው ለመዋጋት አይደለም። ውጊያን ለማስቀረት ነው። ትናንሽ አቅም ይዘው ለሚሳሳቱ ኃይሎች፤ ብዙ ጊዜ [ሰጥተው] እንዲያስቡ ለማስቻል ነው። ውጊያን ለማስቀረት (deter) ለማድረግ ከፍተኛ አቅም ስላለው ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሀገሪቱ እያስፋፋች የምትገኘው አቅም፤ ጦርነት ቢያጋጥም እንኳ “ለማሳጠር የሚያግዙ መሆናቸውን” አብይ ተናግረዋል። “ጦርነት አሳጥሮ ለመጨረስ፤ በቂ ዝግጅት ያስፈልጋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “መዘጋጀት ካልቻልን፤ ጦርነት በማንኛውም ጊዜ ሊያጋጥም እና ሀገር ሊያፈርስ ይችላል። ጦርነት ለማስቀረት በቂ ዝግጅት ያስፈልጋል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

“እንደ ትላንትናው አንለምንም፤ እኛ ነን የምናመርተው። እንደ ትላንትናው አንገዛም፤ እዚሁ ነው የምናመርተው። እንደ ትላንትናው በቁጥር አንያዝም፤ ማባዛት እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጦር መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት “አዳዲስ የጦር አቅሞችን” እና “አቅም አባዢ መሳሪያዎችን ለመታጠቅ” “በትልም መልክ” አስቀምጠው እንደነበር በትላንቱ ገለጻቸው አስታውሰዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት በገባችበት ወቅት እነዚህን መሳሪያዎች በራሷ ገንዘብ ለመታጠቅ ያደረገችው “ሙከራ አለመሳካቱን” እና ግዢም ከጀመረች በኋላ የነበረው ሂደት “ቀላል እንዳልነበር” አስረድተዋል። “ድሮን ገዝተን ለመታጠቅ፤ የምንፈልገውን አይነት፣ የምንፈልገውን ቅርጽ መግዛት እንዳንችል፤ ሻጮችም፣ ሌሎችም ጫና ያሳድሩብን ነበር። በኋላ ተሳክቶልን ድሮን ገዝተን መታጠቅ ስንችል፤ አጠቃቀሙ በፈለግነው ልክ ኦፕሬት ማድረጉ በራሱ ፈተና ነበር” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አብራርተዋል።
ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት፤ ኢትዮጵያ በቻይና፣ ኢራን እና ቱርክ የተሰሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ስትጠቀም መቆየቷን በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያወጧቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች የመከላከያ ሰራዊት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መጠቀም ቀጥሏል።

የመከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በሚያደርጋቸው ወታደራዊ እንስቃሴዎችም፤ የሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱን በተለያዩ ዘገባዎች ላይ ተጠቅሷል። እነዚህን መሰል ጥቃቶቹ ከወታደራዊ ኢላማዎች ይዞታዎች ባሻገር በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም በየጊዜው ሲገልጹ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንቱ ገለጻቸው፤ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ለማጥቃት ብቻ ሳይሆን “የመረጃ አቅምን” ለማሳደግ እና “የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ አውቆ ለማክሸፍ” እንደሚውሉ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ መመረት የጀመሩት የሰው አልባ አውሮፕላኖች “smart sensor” ያላቸው እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (artificial intelligence) የታገዙ መሆናቸውን የጠቀሱት አብይ፤ “ለማጥቃት” እና “ለቅኝት ስራ” እንደሚውሉ አስረድተዋል።
የሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ለመከላከያ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን፤ ለፖሊስ እና ለደህንነት ተቋማት የሚሰጠው የማባዛት አቅም “በጣም ከፍተኛ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። “ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ” የሚያመርታቸው የሰው አልባ አውሮፕላኖች፤ “ለሲቪል አገልግሎት” እንደሚውሉም ተጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)