በቤርሳቤህ ገብረ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ተመራጭ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ተሰማ ዛሬ እሁድ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ተኩል ገደማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለቤታቸው እና የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። አቶ ዮሐንስ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው አስቀድሞ፤ “የጉዞ እግድ እንደተጣለባቸው” ተነግሯቸው ከአሶሳ አየር ማረፊያ እንዲመለሱ መደረጋቸውንም ምንጮቹ ተናግረዋል።
አቶ ዮሐንስ ዛሬ ጠዋት በአሶሳ አየር ማረፊያ የተገኙት፤ ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ ለሆነው ለፌደራል የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ያስገቡትን አቤቱታ በአካል እንዲያስረዱ በመጠራታቸው እንደሆነ ምንጮቹ አስረድተዋል። ለአጣሪ ጉባኤው የቀረበው አቤቱታ፤ ከአቶ ዮሐንስ በተጨማሪ አቶ አመንቴ ገሺ እና አቶ ተስፋሁን ኪሉ የተባሉ የቦዴፓ የክልል ምክር ቤት ተመራጮችን ስም የያዘ ነው።
አቤቱታው ከሁለት ሳምንት በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ የጸደቀውን የክልሉ ህገ መንግስት ማሻሻያ የተመለከተ ነው። የህገ መንግስት ማሻሻያው “የኢፌዲሪን ህገ መንግስት የሚቃረን ነው” ሲሉ በአቤቱታቸው የጠቀሱት፤ ሶስቱ የክልል ምክር ቤት አባላት አጣሪ ጉባኤው የህገ መንግስት ትርጓሜ በመስጠት “ተፈጻሚ እንዳይሆን” እንዲያደርግ ጠይቀው ነበር።

የክልል ምክር ቤት አባላቱ አቤቱታ ማስገባታቸውን ይፋ ካደረጉ ከሁለት ቀናት በኋላ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ቦዴፓን የተመለከተ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ አውጥቷል። ቢሮው በዚሁ መግለጫው፤ “የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች፣ አባሎች እና ደጋፊዎች፤ ክልሉን ዳግም ወደ ግጭት በማስገባት የተሰጣቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ጀምረዋል” ሲል ወንጅሏል።
የቦዴፓ አመራሮች እና አባላት “አዳዲስ አጀንዳዎችን በመፈብረክ እና በተዛባ መንገድ ህዝብ ውስጥ በመበተን፤ ለድብቅ አጀንዳቸው ህጋዊ ሽፋን የመስጠት ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ” ሲልም ቢሮው በዚሁ መግለጫው ከስሷል። ቢሮው “የሞቅታ ዘመቻ” ሲል በጠራው በዚህ እንቅስቃሴ “የሚቀየር አንድም ውሳኔ እንደማይኖር” አጽንኦት ሰጥቶ ነበር።
የፓርቲው አመራሮች ከዚህ ድርጊታቸው “እንዲቆጠቡ” ያሳሰበው የቢሮው መግለጫ፤ የክልሉ መንግስት “ህግንና ስርዓትን ለማስከበር ሲል ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይል” አስጠቅቋል። ይህ መግለጫ ይፋ በሆነበት ዕለት፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህገ መንግስት ማሻሻያ ላይ አቤቱታ ባቀረቡ ሶስት የምክር ቤት አባላት ላይ የጉዞ እገዳ እንዲደረግ የክልሉ መንግስት ለአሶሳ አየር ማረፊያ ደብዳቤ መጻፉን እንደሰሙ የቦዴፓ ምንጮች ገልጸዋል።

የጉዞ እገዳው በትክክልም በክልሉ መንግስት በተጻፈ ደብዳቤ አማካኝነት የተፈጸመ እንደሆነ አቶ ዮሐንስ ዛሬ በአሶሳ አየር ማረፊያ በተገኙበት ወቅት ማረጋገጣቸውን ምንጮቹ አክለዋል። አቶ ዮሐንስ ከአሶሳ አየር ማረፊያ ወደ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት እየተወሰዱ በነበረበት ወቅት አጭር የጹሁፍ መልዕክት ልከውላቸው እንደነበር አንድ የቦዴፓ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የክልል ምክር ቤት አባሉ ከፖሊስ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ወደ መኖሪያ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊስ አባላት በፓትሮል መኪና ጭነው እንደወሰዷቸው እንደተመለከቱም እኚሁ ምንጭ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ለአቶ ዮሐንስ ቅርበት ያላቸው ሌላ ምንጭም ይህንኑ የዓይን እማኙን ገለጻ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
አቶ ዮሐንስ በአሁኑ ወቅት በአሶሳ ከተማ ወረዳ ሁለት በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙም ምንጮቹ ጠቁመዋል። በ1995 ዓ.ም የወጣው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት “ማንኛውም የክልል ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፍቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል።

የክልሉ ህገ መንግስት ከዚህ በተጨማሪ “ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምጽ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፤ አስተዳደራዊ እርምጃም አይወሰድበትም” ይላል። ቦዴፓ የክልል ምክር ቤት ተመራጭ አባሉን እስራት በተመለከተ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በስልክ እንዳሳወቀ የገለጹት የፓርቲው ምንጮች፤ አቤቱታችሁን “በጽሁፍ አቅርቡ” በመባላቸው ይህንኑ የሚያስረዳ ደብዳቤ እያዘጋጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አቶ ዮሐንስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውሉ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። በ2013 ዓ.ም የሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት፤ ከሌሎች ስምንት አባላት ታስረው እንደነበር የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]