ሶስት ከፍተኛ የትግራይ ሰራዊት አዛዦች በአቶ ጌታቸው ረዳ ከስራ ታገዱ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በሶስት የትግራይ ሰራዊት አዛዦች ላይ የስራ እግድ ውሳኔ አስተላለፉ። ፕሬዝዳንቱ ከዛሬ ሰኞ መጋቢት 1፤ 2017 ጀምሮ ከስራ ያገዷቸው ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፤ ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ፣ ሜጀር ጄነራል ማሾ በየነ እና ብርጋዴር ጄነራል ምግበይ ኃይለ ናቸው።

አቶ ጌታቸው የእግድ ውሳኔውን ለጦር አዛዦቹ ያሳወቁት፤ ለእያንዳንዳቸው በዛሬው ዕለት በጻፉት ደብዳቤ ነው። ፕሬዝዳንቱ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትላቸው የሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደንም ጉዳዩን እንዲያውቁት በደብዳቤው ግልባጭ ላይ አካትተዋቸዋል። 

ደብዳቤው የሰላም እና ጸጥታ ካቤኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ከሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ በተጨማሪ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮም ግልባጭ ተደርጓል። ተመሳሳይ ይዘት ያለው የአቶ ጌታቸው ደብዳቤ፤ ቅድሚያ የሰጠው በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ መግለጽን ነው።


“ከመንግስት ውሳኔ ውጪ መላው ህዝባችንን፣ ወጣቶቻችንን ወደ ግርግር፤ የጸጥታ ኃይሎችን ደግሞ ወደ እርስ በእርስ ግጭት የሚከት ብሎም መላው ህዝባችንን ወደማይወጣበት አዘቅት የሚያስገባ እንቅስቃሴ አሁንም አልቆመም” ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ለጦር አዛዦቹ በጻፉት ደብዳቤ ላይ አመልክተዋል። በትግራይ ሰራዊት “የግንባር አዛዦች” ላይ የተላለፈው ውሳኔም ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጥቆማ ሰጥተዋል።

ይህ ሁኔታ “ስርዓት ባለው አካሄድ መግባባት እስኪደርስበት ድረስ”፤ ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ “ከሰራዊት ግንባር የማዘዝ ኃላፊነታቸው” “ላልተወሰነ ጊዜ” የታገዱ መሆኑን አቶ ጌታቸው በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል። ይህ ደብዳቤ በትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን ይፋ ከመደረጉ ጥቂት ሰዓታት በፊት አቶ ጌታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች ለአንድ ቡድን ወገንተኛ ሆነዋል ሲሉ ወንጅለዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት በዚሁ መግለጫቸው፤ የሰራዊት አዛዦቹ ካላቸው ኃላፊነት ውጭ በሆነ አካሄድ ለአንድ ቡድን የመደገፍ እና በህገወጥ አካሄዶች ስልጣንን ለሚፈልጉት ወገን አሳልፎ የመስጠት ዝንባሌዎች እየታዩ መሆኑን አመልክተው ነበር። የጦር መኮንኖቹ ተግባር “የትግራይ ሰራዊትን አንድነትን የሚያደፈርስ” እንዲሁም “የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው” ሲሉም ተችተዋል። 

“የሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች ራሳቸው ያነጹትን ሰራዊት፤ ለተራ አጀንዳ ሲባል እርስ በራሱ የሚፋጠጥበትን ሁኔታ ከመፍጠር መቆጠብ አለባቸው” ሲሉም አቶ ጌታቸው በዚሁ መግለጫቸው አሳስበዋል። “ለኮር አዛዦች፣ ለአርሚ አዛዦች፣ ለግንባር መሪዎች ያለን ክብር እንዳለ ሆኖ፤ አሁን እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው ግን ታሪካቸውን የሚያቆሽሽ፣ ከምንም በላይ ደግሞ የትግራይ ህዝብን ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን አውቀው፣ ስርዓት እና ህግ ባለው መንገድ እንዲሄዱ በዚህ አጋጣሚ መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ” ብለዋል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት።

ሁለት መቶ ገደማ የሚሆኑ የጄነራል እና የኮሎኔል ማዕረግ ያላቸው የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ካደረጉት ስብሰባ በኋላ፤ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ “ለውጦች” እንዲደረጉ የአቋም መግለጫ አውጥተው ነበር። በዚሁ የአቋም መግለጫቸው በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለሚመራው የህወሓት ጎራ እውቅና መስጠታቸው ይታወሳል።

በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ጎራ ይህንን ተከትሎ ባካሄዳቸው ስብሰባዎች እና ባወጣቸው መግለጫዎች፤ የሰራዊት አዛዦቹ ውሳኔዎች እንዲተገበሩ በተደጋጋሚ ግፊት እያደረገ ይገኛል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ በበኩሉ የሰራዊት አዛዦች ያሳለፏቸው ውሳኔዎች፤ “መሰረታዊ ስህተቶች ያለባቸው” እና “ተፈጻሚነት የሌላቸው ናቸው” ሲል ውድቅ አድርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]