በቤርሳቤህ ገብረ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከመንግስት ተቋማት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ ማጠናከሪያ የሚደረግ የገንዘብ ማሰባሰቢያ “በአስቸኳይ ያስቆም” ዘንድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቀረበ። ምርጫ ቦርድ በገዢው ፓርቲ ላይ የሚወስደውን “የእርምት እርምጃ” ለህዝብ “በግልጽ እንዲያሳውቅም” ፓርቲው ጠይቋል።
ኢዜማ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 2፤ 2017 ባወጣው መግለጫ፤ ብልጽግና ፓርቲ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች አንዱ “ፓርቲውን ማጠናከር” እንደነበር አስታውሷል። ይህን ተከትሎም ዜጎች “በውድም ሆነ በግድ የፓርቲ ማጠናከሪያ እንዲያዋጡ እየተደረገ” መሆኑን ኢዜማ “ባሰባሰባቸው ማስረጃዎች” ለማወቅ መቻሉን ገልጿል።
በማንኛውም ፓርቲ ያልታቀፉ ግለሰቦች፤ ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ “ለየትኛውም ድርጅት እና በፈቃደኝት የፈለጉትን ድጋፍ የማድረግ መብት እንዳላቸው” እንደሚገነዘብ ኢዜማ አመልክቷል። ሆኖም ለገዢው ፓርቲ የማጠናከሪያ ገንዘብ እንዲያወጡ እየተገደዱ ያሉት ዜጎች “በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጉዳዮችን ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱበት” ወቅት እንደሆነ ኢዜማ በመግለጫው አብራርቷል።

“ዜጎች አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱባቸው የመንግስታዊ ተቋማት ይህን ተግባር መፈጸም በፍጹም ህገወጥ ተግባር ነው” ሲልም ተቃዋሚ ፓርቲው ነቅፏል። ብልጽግና ፓርቲ አባላቱ ካልሆኑ ዜጎች “ከመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ጋር አያይዞ መዋጮ ማሰባሰብ ምንም ዓይነት የህግም ሆነ የሞራል መሰረት የለውም” ሲልም ተችቷል።
ከተመሰረተ አምስተኛ አመቱን ያስቆጠረው ብልጽግና ፓርቲ፤ የአባላቱ ብዛት 15.7 ሚሊዮን መድረሱን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አብይ አህመድ ባለፈው ወር በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀው ነበር። ብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጋቢት 2014 ባካሄደበት ወቅት ያሉት አባላት 11 ሚሊዮን መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተመሳሳይ መልኩ መግለጻቸው ይታወሳል።
ገዢው ፓርቲ ከዚያ በኋላ ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ የአባላቱ ብዛት በ2.5 ሚሊዮን እንደጨመረ በወቅቱ ይፋ የተደረጉ መረጃዎች አሳይተዋል። ብልጽግና ፓርቲ ይህን መረጃ ካወጣ ከአንድ አመት ከስምንት ወር በኋላ፤ የአባላቱ ብዛት በ2.2 ሚሊዮን ማደጉ ባለፈው ጥር ወር ተመላክቷል።

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው “ብልጽግና [ፓርቲ] ‘በአባላት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ ሆኛለሁ’ የሚለው፤ ይህንን ዓይነት አሳፋሪ ተግባር የሚፈጽሙ አባላቱንም ቆጥሮ ከሆነ፤ መዋቅሩን በድጋሚ ሊያጤነው ይገባል” ሲል አሳስቧል። ብልጽግና ፓርቲ ከመንግስት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ከሚሄዱ እና አባላቱ ካልሆኑ ዜጎች “መዋጮ የሚሰበስበው”፤ “የመንግስት መዋቅርን ለአንድ ፓርቲ አገልግሎት መጠቀም መሆኑን ባለመረዳት” እንዳልሆነ ኢዜማ በመግለጫው አስፍሯል።
ይልቁንም ይህ አይነቱ የገዢው ፓርቲ ድርጊት “የማናለብኝነት ስሜቱ የት እንደደረሰ” እንደማሳያ የሚወሰድ መሆኑን ኢዜማ አትቷል። “በሀገራችን ‘የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ይኑር’ የሚል ‘ቁርጠኛ አቋም አለኝ’ የሚል ፓርቲ፤ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ውስጥ መገኘቱ ዓይን ያወጣ አድልኦ እየሠራ መሆኑ ሊያወቀው ይገባል” ሲልም ኢዜማ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።
“ገዢው ፓርቲ አሁን አለኝ ከሚለው ግዝፈት በላይ ለመለጠጥ የሚሄድበት መንገድ፤ ቅጥ ያጣ እራስ ወዳድነት እና አልጠግብ ባይነትን የሚያሳይ ነው” ሲልም ኢዜማ ተችቷል። “በዚህ መንገድ የምንጓዝ ከሆነ በሀገራችን ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫም ይደረጋል ብሎ ማሰብ ዘበት ይሆናል” በማለትም ጉዳዩ ከአንድ አመት በኋላ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ጭምር ተጽእኖ እንደሚኖረው ኢዜማ አስጠንቅቋል።
“ገዢው ፓርቲ አሁን አለኝ ከሚለው ግዝፈት በላይ ለመለጠጥ የሚሄድበት መንገድ፤ ቅጥ ያጣ እራስ ወዳድነት እና አልጠግብ ባይነትን የሚያሳይ ነው። በዚህ መንገድ የምንጓዝ ከሆነ በሀገራችን ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫም ይደረጋል ብሎ ማሰብ ዘበት ይሆናል”
– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
በአሁኑ ወቅት ዜጎች “በኑሮ ውድነት በሙስና በመልካም አስተዳደር እጦት” እየተንገላቱ መሆኑ በመግለጫው የጠቀሰው ተቃዋሚ ፓርቲ፤ በዚሁ ሁኔታ “በጠራራ ጸሀይ በፓርቲ መዋጮ ስም የሚፈጸም ዝርፊያ በቸልታ የሚታለፍ” እንዳልሆነ አስገንዝቧል። ዜጎችም ይህን አካሄድ “በግልጽ እምቢ” እንዲሉም ጥሪውን አቅርቧል።
ብልጽግና ፓርቲ “በተደጋጋሚ መንግስት እና ፓርቲን መለየት ሲሳነው ማስተዋሉን” ኢዜማ በዛሬው መግለጫ መጀመሪያ ላይ ቢጠቅስም፤ በመግለጫው ማጠቃለያ ደግሞ መንግስት “ስርዓት እንደዲያስከብር” ጠይቋል። ኢዜማ በመግለጫ ማጠቃለያው ላይ “ድርጊቱን የሚፈጽሙ” የብልጽግና ፓርቲ አባላትም “ከህገወጥ ስራቸው እንዲታቀቡ” አሳስቧል።
ኢዜማ በዛሬው መግለጫው ማገባደጃ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህግ መሰረት መስራታቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣን በአዋጅ ለተሰጠው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ጥሪ አቅርቧል። የመንግስት ተቋማት ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች “ለብልጽግና ፓርቲ ማጠናከሪያ” የሚሰበስቡትን ገንዘብ፤ ምርጫ ቦርድ “በአስቸኳይ እንዲያስቆም”ጠይቋል።

ቦርዱ በብልጽግና ፓርቲ ላይ የሚወስደውን “የእርምት እርምጃም” ለህዝብ “በግልጽ እንዲያሳውቅ” ኢዜማ ጥያቄ አቅርቧል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፤ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ “ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የመንግስት ከሆኑ የልማት ድርጅቶች” የሚቀርብለትን “ስጦታ ወይም እርዳታ መቀበል አይችልም” ሲል ይደነግጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)