ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ እንዲያሸማግሏት ለአሜሪካ፣ ለቻይና እና ሩሲያ ጥያቄ ማቅረቧን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ  

ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጉዳይን በተመለከተ ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለሩሲያ እና ለበርካታ ሀገራት “እንዲያሸማግሏት” እና “መፍትሔ እንዲያመጡ” ጥያቄ ማቅረቧን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በቀይ ባህር ምክንያት “ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ውጊያ ከተነሳ ግን ውጤቱ “ግልጽ” እንደሆነ እና ሀገሪቱን “ማንም እንደማይስቆማት” አስጠንቅቀዋል።

አብይ ይህን ያሉት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 18፤ 2018 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአካል ተገኝተው፤ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ላይ ነው። በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የባህር በር እና የቀይ ባህርን የተመለከቱት ይገኙበታል። 

የቀይ ባህር ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ የማቅረብ ዕድል ካገኙ 19 የፓርላማ አባላት መካከል በአራቱ ተነስቷል። ጉዳዩን ከኤርትራ ጋር ባለው ግንኙነት ውስጥ እንዴት እንደሚታይ የጠየቁ ሁለት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት፤ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መድረክ ስለ ሀገሪቱ ሲነሳ ከሚነገርበት አካሄድ በተለየ መልኩ የኤርትራን ገዢው ፓርቲ “ሻዕቢያ” በሚል ስያሜ ሲጠሩት ተደምጠዋል። 

ከእነሱ አንዱ የሆኑት በተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ቋሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሂ፤ ሻዕቢያ “ጸረ ሰላም ኃይል” ነው ብለዋል። “የሻዕቢያ ቡድን የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ጥያቄ ለማዛባት፣ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ እና የሚያሰራጩ ኃይሎችን አሰማርቷል። በሀገራችን ውስጥ ግጭቶች እንዲባባሱ ተግቶ ከመስራት ጀምሮ የተለያዩ አፍራሽ ሙከራዎችን እያደረገ ይገኛል” ሲሉ ዶ/ር ቶፊቅ ወንጅለዋል። 

የፓርላማ አባሉ “የሀገር ሉዓላዊነትን የሚጥስ” ያሉትን “የሻዕቢያ እኩይ ተግባር” እና “የሽብር ድርጊት” የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ በመንግስት በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ጠይቀዋል። የዓለም ጤና ምርጫ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ ጫላ ለሚ በበኩላቸው፤ “ከህግ እና ስርዓት ባፈነገጠ መንገድ” ይንቀሳቀሳል ያሉት የህወሓትን ቡድን፤ ከሻዕቢያ ጋር በማበር ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን በመጥቀስ ነቅፈዋል። 

“አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የህወሓቱ የአዛውንቶች ቡድን ከሻዕቢያ ኃይሎች ጋር ግንባር ፈጥረው ለጥፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይሰማል። በመሆኑም ሉዓላዊነታችንን የሚዳፈር የሻዕቢያ እንቅስቃሴ ለመግታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ቢሰጡ” ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።

ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የፓርላማ አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ቀይ ባህርን የማስመለስ ጉዳይ “እንደህልውና ጉዳይ” ማቅረቡን በተመለከተ አስተያየት እና ጥያቄያቸውን ሰንዝረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት “ዋና ትኩረቱን” እና “የፖለቲካ ጉልበቱን” አጣዳፊ የውስጥ ቀውሶችን ከመፍታት ይልቅ በውጭ ጉዳይ ላይ እንዲያርፉ ማድረጉ “ ‘የህዝብን ትኩረት ለመቀየር የተደረገ ጥረት ነው’ የሚል አስተያየት እንዲሰጥ አድርጓል” ብለዋል የፓርላማ አባሉ። 

“በሀገሪቱ ውስጥ ካለው የውስጥ ችግሮች ክብደት አኳያ መንግስት ይህንን ከፍተኛ የፖለቲካ አቅም ለውጫዊ ግብ እና ዓላማ ከማዋል ይልቅ ተመሳሳይ ጉልበት እና ትኩረት የውስጥ የፖለቲካ ግጭቶችን ለመፍታት እና ከራሱ ዜጎች ጋር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ለምን አይጠቀምበትም?” ሲሉም ዶ/ር ደሳለኝ ጠይቀዋል።

“ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረግ ማንኛውም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን በግሌ እቀበለዋለሁ” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ “መንግስት ጉዳዩን የመራበት መንገድ ግን አስር ድስት ጥዶ አንዱንም ሳያማስል እንደሚያሳርረው አይነት ነው” ሲሉ ተችተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ወደብ መጠቀምን በተመለከተ ከኤርትራ፣ ከሶማሌላንድ፣ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ስምምነት ማድረጉን መግለጹን፤ ዶ/ር ደሳለኝ ለዚህ አባባላቸው በማስረጃነት አቅርበዋል።

“አሁን ደግሞ ከኤርትራ ጋር በጦርነት ዋዜማ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል። በሁለቱ ሀገራት በኩል የተሟላ የጦርነት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በሰፊው ተሰግቷል” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ “የባህር በር ጉዳይን አስመልክቶ ከኤርትራ ጋር የገባንበትን እሰጣ እገባ በሰላማዊ፣ ህጋዊ እና ሰጥቶ መቀበልን መሰረት ባደረገ አካሄድ ብቻ እንዲፈታ እጠይቃለሁ” ሲሉ የፓርላማ አባሉ አቋማቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከቀይ ባህር እና የባህር በር በተያያዘ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የጀመሩት የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይን በማንሳት ነው። “ሁሉም ሀገር መጠኑ ይነስም ይብዛ፣ ሀብቱ ይብዛ ይነስም፤ ሁሉም ሀገር የተፈጥሮ ጸጋውን ሌላውን ሳይጎዳ የመጠቀም መብት አለው። ተፈጥሮ ያደለችውን ሀብት በሌላ ላይ ጉዳት ሳያመጣ መጠቀም የሁሉም ሀገር መብት ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚመለከት “ኢ-ርትዓዊ”፣ “ኢ-ፍትሃዊ” እና “የበደል የመጨረሻው በደል” የተፈጸመባት ሀገር መሆኗን አብይ በማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል። ይህን ጉዳይ ለመናገር ክልከላ ሊደርግባቸው እንደማይገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢ-ፍትሃዊ እና ኢ-ርትዓዊ ውሳኔ ባለበት ሁኔታ “የተሟላ ሰላም ሊፈጠር” እንደማይችል አስገንዝበዋል። 

“ጦርነት የለም ማለት የተኩስ ድምጽ አይሰማም ማለት አይደለም። እውነተኛ ፍትህ ካልተረጋገጠ በማንኛውም ሰዓት ጦርነት ሊፈጠር ይችላል”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

“ጦርነት የለም ማለት የተኩስ ድምጽ አይሰማም ማለት አይደለም። እውነተኛ ፍትህ ካልተረጋገጠ በማንኛውም ሰዓት ጦርነት ሊፈጠር ይችላል” ሲሉም አብይ አክለዋል። ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላት ጥያቄ “ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልዕክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ  ነው ብለን እናምናለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ጉዳይ ከውጊያ ይልቅ “በህጋዊ መንገድ” እና “በንግግር ሊፈታ ይችላል” የሚለውን አቋማቸውን በማብራሪያቸው ደጋግመው አንጸባርቀዋል። 

“ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለማጣት 30 ዓመት ከዚያ በላይ የወሰደ ትግል ነበር። በ30 ዓመት ትግል ውስጥ በብዙዎች ርብርብ ነው ኢትዮጵያ ያጣችው። ሌላ 30 ዓመት ያስፈልጋታል ብዬ ግን አላስብም። በተረጋጋ መንገድ፣ በሰከነ መንገድ፣ በውይይት መሄድ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። የፈለገ ብንወያይ ግን ለማጣት የፈጀውን 30 ዓመት፣ ለማግኘት ይፈጅብናል ብዬ ግን አላስብም” ሲሉም ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጠው “ለሰላም” እና “ንግግር” መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ሀገሪቱ ቀይ ባህርን መጠቀሟ “አይቀሬ” ስለሆነ በጉዳዩ ላይ እንዲያሸማግሏቸው ለበርካታ ሀገራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። “የሽምግልና” እና “የመፍትሔ አምጡልን” ጥያቄ ከቀረበላቸው ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ እንደሚገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። 

ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለሌሎች የአውሮፓ እና የአፍሪካ ሀገራት እንደቀረቡ አብይ በማብራሪያቸው ቢያነሱም፤ ማንነታቸውን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል። ይህን ጥያቄ የሚቀበሉ ሀገራት፤ “አዎ እንሸመግላችኋላን፣ ሰላም ያስፈልጋል እያሉ ማዘናጋት ከሆነ ግን ጉዳዩ ብዙ የሚሄድ አይመስለኝም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሸማገል ፍላጎት ላላቸው አካላት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የነበራትን “የባህር በር በአንድ ቀን እንዳላጣቸው ሁሉ፤ በአንድ ቀን እንደማትመልሰው” ያስገነዘቡት አብይ፤ ጉዳዩ ተፈጥሯዊ ሂደቱን ተከትሎ የሚሄድ በመሆኑ እንደማይቆም ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ቀይ ባህር እንደሚያስፈልጋት ከለውጡ በፊትም እናምን ነበር። እንናገር ነበር። ያኔ መደመጥ አንችልም። ከጀመርንበት ቀን አንስቶ ግን ንግግሩ አለ። ያ ንግግር ግን ሰላማዊ መሆን አለበት” ሲሉም አብይ በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊትም የሚያቀነቅኑት እንደነበር አስረድተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም በነበራቸው የፓርላማ ተመሳሳይ ስብሰባዎች ላይ ሲናገሩ እንደተደመጠው፤ ዛሬም “ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለንም” ሲሉ ደጋግመው ማረጋገጫ ለመስጠት ሲሞክሩ ተስተውለዋል። በዚህ ማረጋገጫቸው ላይ የኤርትራን ህዝብ በስም ጠቅሰውም አንስተዋል።

“የኤርትራ ህዝብ አሁንም ወንድም ህዝብ ነው። ምስኪን ህዝብ ነው። ሀገሩን ለቅቆ እየተሰደደ ያለ ህዝብ ነው። ከዚህ ህዝብ ጋር በጋራ መስራት፣ መተባበር ፍላጎታችን ነው። በፍጹም የውጊያ መሻት የለንም” ብለዋል አብይ። “ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለንም። ለምን? ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሰራም። አሁን አለመጀመር ነው” ሲሉም ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግራቸውን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት አስተላልፈዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጊያ ቢቀሰቀስ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጊዜያት አጋዥ ሀገራት እና ኃይሎች እንደማይኖሩ አበክረው አሳስበዋል። ከዚህ ቀደም በተካሄደ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ለትግራይ ኃይሎች የሰጡትን ማሳሰቢያም፤ ከቀይ ባህር ጋር በሰጡት ማብራሪያ ላይ በድጋሚ ተጠቅመውታል። 

“አሁን ውጊያ እንትና ያግዘኛል፣ እንትና የሚባል ነገር [የለም]። ሰው እንዴት ዩክሬንን እያየ፣ ፍልስጤምን እያየ ስለማገዝ ያወራል። ማንም አይሞትልህም። ሞራል ይሰጥሃል እንጂ አይሞትልህም። መጨረሻ የምትሞተው አንተ ነህ። አያዋጣም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ “ውጊያ” “በቲፎዞ እንደማይቆምም” አብይ በአጽንኦት አንስተዋል።

“ከማንም ጋር ግጭት ለማድረግ ፍላጎት የለንም። ከገባን ግን ግልጽ ነው ውጤቱ። አስተማማኝ አቅም ነው ያለን። ማንም አያቆመንም። ይሄ ግልጽ ነው መሆን ያለበት። ማንም አያቆመንም። ወደዚያ እንዳንሄድ በኃላፊነት መስራት አስፈላጊ ይመስለኛል”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

“ከማንም ጋር ግጭት ለማድረግ ፍላጎት የለንም። ከገባን ግን ግልጽ ነው ውጤቱ። አስተማማኝ አቅም ነው ያለን። ማንም አያቆመንም። ይሄ ግልጽ ነው መሆን ያለበት። ማንም አያቆመንም። ወደዚያ እንዳንሄድ በኃላፊነት መስራት አስፈላጊ ይመስለኛል” ሲሉም አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)