በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ያለው “መካረር” ዳግም ወደ ጦርነት ያመራል የሚል “ከፍተኛ ስጋት” እንዳለው የገለጸው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት፤ ጉዳዩ “በንግግር” እና “በድርድር” እንዲፈታ ጥሪ አቀረበ። ድርጅቱ መንግስት በትግራይ ክልል ያሉትን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ተፈናቃዮች የመመለስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል።
ሀገር በቀል የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋሙ ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 24፤ 2018 አዲስ አበባ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ድርጅቱ የዛሬውን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው፤ ተቀማጭነታቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ከሆነው “ትግራይ አካውንተብሊቲ ኮአሊሽን” (Tigray Accountability Coalition) ጋር በመተባበር መሆኑን ገልጿል።
ጋዜጣዊ መግለጫው የተዘጋጀው፤ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት ያህል የቆየው ጦርነት የተጀመረበት አምስተኛ ዓመት እንዲሁም የፕሪቶሪያ ስምምነት የተፈረመበትን ሶስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መሆኑንም ድርጅቱ ጠቅሷል። በጥቅምት 24፤ 2013 የተቀሰቀሰው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በይፋ የተቋጨው፤ የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ተወካዮች በደቡብ አፍሪካዊቷ ፕሪቶሪያ ከተማ ጥቅምት 23፤ 2015 ግጭት የማቆም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነበር።
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ያስከተለውን “በጣም ሰፊ የሰው እልቂት፣ የኢኮኖሚ ውድመት እንዲሁም ሰፊ ማህበራዊ ቀውስ” በማስቆሙ በአዎንታ እንደሚመለከቱት የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋአለም በርሀ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አመልክተዋል። የሚመሩት ድርጅት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረቱ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ባለው “መካረር” ሳቢያ በድጋሚ ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል “ከፍተኛ ስጋት” እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የህወሓት ህጋዊነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሰረዙን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረው “ክፍፍል” እነ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎች የቀድሞ የህወሓት አባላት አዲስ ፓርቲ መመስረታቸውን ጠቅሰዋል። ክፍፍሉን “ፖለቲካ የወለደው” ሲሉ የጠሩት አቶ ተስፋአለም፤ ለችግሩ “ትክክለኛ መፍትሔ” ለማምጣት በትግራይ ክልል ካለው ኃይል ጋር “ድርድር” መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ውጊያዎች “ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያስከተሉ” መሆኑን በተጨማሪነት ያነሱት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር፤ በሁለቱ ክልሎች ያሉ ችግሮች “በንግግር እና በውይይት እንዲቋጩ” ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። የሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃን እና መላው ማህበረሰብ፤ “ጦርነት አያስፈልግም” የሚል ዘመቻ እንዲጀምሩም ጠይቀዋል።

ጦርነት እና ውጊያዎች ከሚያስከተሏቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሌላ በርካታ ሰዎችን ለመፈናቀል እንደሚዳርጉም በዛሬው መግለጫ በአጽንኦት ተነስቷል። የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ያወጣውን አሃዝ በመጥቀስ በትግራይ ክልል ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ የገለጹት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር፤ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግስት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
የተፈናቃዮች ወደ ቀደመ መኖሪያቸው መመለስ፤ በፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ውስጥ ተግባራዊ እንዲደረጉ ከተዘረዘሩ ጉዳዮች አንዱ ነው። አቶ ተስፋአለም የፕሪቶሪያው ስምምነት ባይኖርም የፌደራል መንግስት በፈረማቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ባጸደቃቸው ህጎች መሰረት መንግስት ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ኃላፊነቱን “የመፈጸም” እና “የማስፈጸም ግዴታ” አለበት ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን የመጠበቅና ድጋፍ የማድረግ የሚያስገድደውን የአፍሪካ ህብረት የካምፓላ ኮንቬንሽን ተቀብላ ያጸደቀችው በየካቲት 2012 ዓ.ም ነው። በጥቅምት 2002 ዓ.ም የወጣውን ይህንን ኮንቬንሽን ኢትዮጵያ ከማጽደቋ አስቀድሞ 30 የአፍሪካ ሀገራት በየፊናቸው በህግነት ተቀብለውት ነበር።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ ህግ ማጽደቁን ተከትሎ በመጋቢት 2012 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ፤ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ መንስኤዎች የሚደርስ መፈናቀልን በተመለከተ መንግስት የሚኖርበት ግዴታ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ በተደነገገው መሰረት እንደሆነ ያስቀምጣል። በአዋጁ የተጠቀሰው የህገ መንግስት ድንጋጌ፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ሲደርስ መንግስት “ለተጎጂዎች እርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ ማድረግ” እንዳለበት የሚያትት ነው።
በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ተፈናቃዮችን መንግስት ወደ ቀያቸው “የመመለስ ግዴታ አለበት” የሚሉት የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር፤ ህጎችን በማጣቀስ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት የሚወስዱት መሆኑን ገልጸዋል። “አንደኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህጎችን የማስፈጸም ግዴታ [አለበት]። ሁለተኛ የሰላም ሚኒስቴር የካምፓላ ስምምነትን ለማስፈጸም ኃላፊነት ወስዷል። ሶስተኛ የክልል መንግስታት፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እነዚህ አካላት ድርሻ ያላቸው በመሆናቸው ወደ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን” ብለዋል አቶ ተስፋአለም።
በ2011 ዓ.ም. የተቋቋመው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ፤ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል ሰብአዊ መብቶችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ መፍትሔ ማስገኘት የሚለው አንዱ ነው። ድርጅቱ ሰብአዊ መብቶችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትምህርት መስጠት፣ የአድቮከሲ ስራዎችን ማከናወን፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር እና ሪፖርቶችን ማውጣት የሚሉት ሌሎች ዓላማዎቹ ናቸው።

ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ድርጅት የተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚያቀርበው፤ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ ችሎት፣ መሰረታዊ መብቶች ችሎት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። “ሊፈጸምም ላይፈጸምም ይችላል። በነገራችን ላይ ዋናው ነገር ድምጽ መሆኑ ነው። የእነዚህ የተፈናቃዮችን ጉዳይ ወደ ጠረጴዛ ማምጣት ነው” ሲሉ አቶ ተስፋአለም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































