ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሰው አልባ አውሮፕላን “ድብደባ በመፈጸም” በትግራይ ሰራዊት አባላት እና በአካባቢው ባሉ በነዋሪዎች ላይ “ጉዳት አድርሷል” ሲል ወነጀለ። ህወሓት በዛሬው ዕለት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ በጻፈው ደብዳቤ፤ “የድሮን ጥቃቱ” የፕሪቶሪያ ስምምነትን “በግልጽ የጣሰ ነው” ብሏል።
ፓርቲው ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫም ይህንኑ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያን ስምምነት “በግልጽ ወደ መጣስ ተሸጋግሯል” ሲል በደብዳቤው ላይ የጠቀሰውን አቋም አስተጋብቷል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅናው ባለፈው ግንቦት ወር የተሰረዘው ህወሓት፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት ለመጣሱ ማሳያ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በመግለጫው ዘርዝሯል።
በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን “በማደራጀት” እና “በማስታጠቅ” የኢትዮጵያን መንግስት የከሰሰው ህወሓት፤ ይህን የሚያደርገው “ትግራይን የማፍረስ” ስትራቴጂውን ለማሳካት እና የክልሉ ህዝብ “እርስ በእርስ እንዲጠፋፋ” በማሰብ እንደሆነም ወንጅሏል። እነዚህን ታጣቂዎች በመጠቀም “ሌላ ዙር ጦርነት ለመክፈት”፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል ሰፊ የማደናገሪያ ስራ እየሰራ ነው” ሲል ህወሓት በመግለጫው ከስሷል።

ህወሓት በመግለጫው “በጥቂት ከዳተኞች የተታለሉ” እና “ሽፍቶች” ሲል የጠራቸው ታጣቂዎች፤ በቅርብ ጊዜ በራያ አዘቦ ወረዳ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ከፍተው እንደነበር ጠቅሷል። ፓርቲው ለተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዛሬው ዕለት በጻፈው ደብዳቤም፤ “በፌደራል መንግስቱ ይደገፋሉ” ያላቸው ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ፈጽመውታል ያለውን ድርጊት አንስቷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ደቡብ ትግራይ ለስራ ባቀኑበት ወቅት፤ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ታጣቂዎች ጉብኝቱን ማስተጓጎላቸውን እና የልዑካን ቡድኑን ደህንነት ለአደጋ ማጋለጣቸውን ህወሓት በደብዳቤው አትቷል። ከዚህ ሁነት በኋላ የታጣቂዎቹ ቡድኑ ከትግራይ ጋር “በግልጽ ግጭት” ውስጥ እንዳለ “ማወጁን” እና የፌደራል መንግስትም “ለእንቅስቃሴዎቹ ድጋፍ እንዲያደርግለት” በይፋ መጠየቁ በህወሓት ደብዳቤ ተጠቅሷል።
የፌደራል ኃይሎች “ለዚህ ጥያቄ ምላሽ በሚመስል መልኩ”፤ ትላንት ሐሙስ ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ገደማ ላይ በትግራይ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸማቸውን ህወሓት ለተመድ ዋና ጸሀፊ በላከው ደብዳቤ ከስሷል። ህወሓት ዛሬ ምሽት በትግርኛ ቋንቋ ባሰራጨው መግለጫው፤ “የድሮን ድብደባው በትግራይ ሰራዊት አባላት እና በአካባቢው ባሉ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል” ሲል ወንጅሏል።

“የድሮን ጥቃቱ” “ጠመንጃዎችን ጸጥ የማሰኘት እና ልዩነቶችን በውይይት መፍታት” የሚለውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ዋና መርህ “በግልጽ” የጣሰ መሆኑን ህወሓት ለጉተሬዝ በጻፈው ደብዳቤ ላይ አመልክቷል። ይህ “ጥቃት” እና በቅርቡ የተፈጸሙ ድርጊቶች፤ በቋፍ ላይ ያለውን የትግራይ ክልል ሰላም “ለአደጋ የሚያጋልጡ” እና የቀጠናውን መረጋጋት “የሚያዳክሙ” መሆናቸውን ህወሓት በደብዳቤው በአጽንኦት አንስቷል።
ፓርቲው የፕሪቶሪያ ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር እና በፖለቲካዊ ውይይት ሰላምን ለመሻት “የማያወላውል ቁርጠኝነት” እንዳለውም ለተመድ ዋና ጸሀፊ ገልጿል። የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ግጭቶችን” እንዲያቆም፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት የገባቸውን “ግዴታዎች እንዲያከብር”፣ “በቅን ልቦና ለሚደረግ ለውይይት” በድጋሚ እንዲዘጋጅ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት እንዲያደርጉም ህወሓት በደብዳቤው ጥሪ አቅርቧል።
ህወሓት ያቀረበውን ውንጀላ በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም። የአፋር ክልል መንግስት ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ “የህወሓት ቡድን” ረቡዕ ጥቅምት 26፤ 2018 የክልሉን ወሰን ተሻግሮ በመግባት “በከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙን” እና “ስድስት መንደሮችን መቆጣጠሩን” በመግለጽ ወንጅሎ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































