በተስፋለም ወልደየስ
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከትላንት ማክሰኞ ግንቦት 5፤ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። የምስረታውን የወርቅ ኢዮቤልዮ ባለው የካቲት ወር ያከበረው ህወሓት ከፓርቲነት የተሰረዘው፤ ቦርዱ ያዘዘውን “የእርምት እርምጃ” ተግባራዊ ባለማድረጉ መሆኑን ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ለፓርቲው የሰጠው ቀነ ገደብ በዛሬው ዕለት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው። ቦርዱ ይህንን ቀነ ገደብ ባሳወቀበት መግለጫው፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችል “የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን” በሶስት ወራት ውስጥ እንዲያካሄድ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ቦርዱ ህወሓትን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄድ ያዘዘው፤ “በአመጽ እና በህገ- ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ” የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን “በልዩ ሁኔታ” እንደሚዘገቡ የሚያስችለው አዋጅ በሚያስቀምጠው ድንጋጌ መሰረት ነው። ይህ አዋጅ “በልዩ ሁኔታ” የሚመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያካሄዱ በምርጫ ቦርድ ሊታዘዙ እንደሚችሉ ይደነግጋል።
ይህን አዋጅ መሰረት በማድረግ በነሐሴ 2016 ዓ.ም ለህወሓት የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሰጠው ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲው “የቦርዱ ታዛቢዎች” በተገኙበት በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር። ቦርዱ የቅደመ ጉባኤውን የዝግጅት ስራዎች ለመከታተል እንዲረዳው፤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማካሄዱ 21 ቀናት በፊት ለመስሪያ ቤቱ እንዲያስታውቅም ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ጎራ በበኩሉ፤ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት የሰጠው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫን ባለመቀበል የራሱን ጠቅላላ ጉባኤ በነሐሴ ወር አካሄዷል። ይህ የህወሓት ጎራ የምርጫ ቦርድን የምስክር ወረቀት ውድቅ ያደረገው፤ የፓርቲውን የቀድሞ ህልውና “ወደነበረበት የማይመልስ ነው” በሚል ምክንያት ነበር።
ያለ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና በተካሄደው በነሐሴው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ፤ ዶ/ር ደብረጽዮን ፓርቲውን እንዲመሩ በድጋሚ መመረጣቸው የሚታወስ ነው። ህወሓት በአዋጅ እና በመመሪያ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ባለማክበር ሲያደርጋቸው የነበሩ እነዚህን መሰል እንቅስቃሴዎች፤ “ጉልህ የህግ ጥሰት” መፈጸሙን የሚያሳዩ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት ወር ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

በዚህም ምክንያት ፓርቲው ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለሶስት ወራት ታግዶ እንዲቆይ እና ለእግዱ ምክንያት የሆነውን ጥሰት በዚሁ ጊዜ ውስጥ እንዲያርም ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ህወሓት በሶስት ወራት የእግድ ጊዜው ውስጥ “የእርምት እርምጃ” ካልወሰደ፤ ምርጫ ቦርድ “የተለየ አካሄድ ሳይከተል” የፓርቲው ምዝገባ እንዲሰረዝ እንደሚያደርግም በዚሁ መግለጫው አስጠንቅቆ ነበር።
በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ጎራ ባለፈው አርብ ባወጣው መግለጫ፤ ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው መግለጫዎች “እኔ ያልኳችሁን ብቻ ስሙ” የሚል መልዕክት ያላቸው እና “ዛቻ አዘል” ናቸው ሲል ኮንኗል። ምርጫ ቦርድ “ነባሩን ህጋዊ የዕውቅና ሰርተፊኬት ሳይመልስ ‘እሰርዛለሁኝ’ ማለቱ፤ ትርጉም አልባ ነው” ያለው ፓርቲው፤ መስሪያ ቤቱ ህወሓትን ሊያስተዳደር የሚችለው ፓርቲው በጠየቀው መሰረት “ነባሩን ዕውቅና ሲሰጥ ብቻ” እንደሆነ ገልጾ ነበር።
ምርጫ ቦርድ በነሐሴ 2016 ዓ.ም ለፓርቲው የሰጠውን እና በእነርሱ በኩል ተቀባይነት ያላገኘውን ሰርተፍኬት የሚሰርዝ ከሆነ ግን “ያንን ማድረግ እንደሚችል” ይኸው የህወሓት ጎራ በመግለጫው አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 6፤ 2017 ባወጣው መግለጫ፤ ፓርቲው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫውን “በወቅቱ አምኖበት እና ተስማማቶ የተቀበለው” መሆኑን ገልጿል።

ህወሓት “በልዩ ሁኔታ” የሚመዘገቡ ፓርቲዎች በህግ እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸውን ሰነዶችም፤ በሐምሌ 19፤ 2016 ለምርጫ ቦርድ ማስገባቱንም መስሪያ ቤቱ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። ሰነዶቹ የፓርቲውን ፕሮግራም፣ የመተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲውን አመራሮች ስም ዝርዝር ከፊርማ ጋር የያዙ መሆናቸውንም ቦርዱ አመልክቷል።
ፓርቲው በሐምሌ 2016 ዓ.ም. “በልዩ ሁኔታ” ለመመዘገብ ጥያቄ ሲያቀርብ፤ “በአመጽ እና በህገ- ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ” የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ እንደሚዘገቡ የሚያስችለው አዋጅ ስራ ላይ ከዋለ ሁለት ወር ያለፈው መሆኑንም መስሪያ ቤቱ ጠቅሷል። ምርጫ ቦርድ የጠቀሰውን አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው በግንቦት 2016 ዓ.ም. ነበር።
“በዚህ ወቅት የአዋጁ አላማ፣ አፈጻጸም እና በአዋጁ መሰረት ‘በልዩ ሁኔታ’ ፓርቲ ሆኖ የመመዝገብ ሂደት በግልጽ የታወቀ በመሆኑ፤ ህወሓትም ይህንኑ ለህዝብ ይፋ የሆነውን አዋጅ አላማና አፈጻጸም በግልጽ በማወቅ እና በመረዳት፤ በአዋጁ ላይ የተመለከቱትን ሰነዶች አያይዞ በማቅረብ፤ በአዋጁ የተጠየቀውን የምዝገባ ስርዓት በመፈጸም ምዝገባው ተከናውኗል” ሲል ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው አብራርቷል።

ህወሓት በሐምሌ 2016 ዓ.ም ለምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ “የቀድሞው ህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ” የሚል ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወሰው ቦርዱ፤ ሆኖም ፓርቲው አያይዞ ያቀረባቸው ሰነዶች እና ጥያቄው የቀረበበት ጊዜ የአዋጁን መውጣት ተከትሎ መሆኑ ሊታይ እንደሚገባ ገልጿል። የህወሓት ይኸው ደብዳቤ፤ ፓርቲው በ“ልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገብ ፍትሕ ሚኒስቴር ለቦርዱ ደብዳቤ መጻፉን የሚያስረዳ መሆኑንም አመልክቷል።
ምርጫ ቦርድ ለዚህ ደብዳቤ በሰጠው ምላሽ፤ የህወሓት የቀድሞው ህጋዊ ሰውነት “እንደማይመለስለት” “በግልጽ” ማመልከቱንም አስታውሷል። ከዚህ ምላሽ በኋላ “የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ሰርተፊኬቱን እና ደብዳቤውን በሚገባ አይተው፣ አንብበው እና ተስማምተው፣ በፍቃዳቸው ፈርመው ከወሰዱ በኋላ ‘ይህ ‘በልዩ ሁኔታ’ ተመዝግቦ የተሰጠን የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫን አንቀበለውም’ ማለት ተቀባይነት የለውም” ሲል ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው ላይ አስፍሯል።
“በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት” እና ህወሓት ያለበትን “ኃላፊነት እና ግዴታ እንዲወጣ ለማድረግ”፤ ምርጫ ቦርድ በተለያየ ወቅት በጹሁፍ ማሳሰቢያ ሲሰጥ መቆየቱን ገልጿል። ህወሓት “ግዴታውን ባለመወጣቱ”፤ ቦርዱ “ምንም አይነት ቅደመ ሁኔታ ሳይጠብቅ” ፓርቲውን መሰረዝ የሚያስችል የህግ መሰረት እንደነበረውም መስሪያ ቤቱ በመግለጫው አስታውሷል።
“የህወሓት ከፍተኛ አመራር በቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ሰርተፊኬቱን እና ደብዳቤውን በሚገባ አይተው፣ አንብበው እና ተስማምተው፣ በፍቃዳቸው ፈርመው ከወሰዱ በኋላ ‘ይህ ‘በልዩ ሁኔታ’ ተመዝግቦ የተሰጠን የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫን አንቀበለውም’ ማለት ተቀባይነት የለውም”
– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ምርጫ ቦርድ “ፓርቲው ግዴታውን እንዲወጣ” በሚል፤ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ “የእርምት እርምጃ” እንዲወስድ “ጥረት ማድረጉንም” ገልጿል። ሆኖም ህወሓት “የተጣለበትን የህግ ግዴታ ለመወጣት ፍቃደኛ ባለመሆኑ” እና በቦርዱ የታዘዘውን “የእርምት እርምጃ” ባለመውሰዱ ከግንቦት 5፤ 2017 ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]