የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይ ክልል ኃይሎች “ወደ አፋር ክልል ዘልቀው ጥቃት ፈጽመዋል” መባሉን አስተባበለ። የአፋር ክልል ይህንኑ በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ “መስረተ ቢስ” ሲል ያጣጣለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በትግራይ በኩል የሚፈጠር “ሁከትም” ይሁን “አለመረጋጋት” እንዲኖር “በፍጹም እንደማይፈልግም” ገልጿል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን ያለው ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 27፤ 2018 ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ ነው። ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚሁ መግለጫው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ ሂደቶችን የሚያውኩ” እና “የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የሚጎዱ” ያላቸውን “እንቅስቃሴዎች” እየተመለከተ መሆኑ አስፍሯል።
የትግራይ ክልልን ሆን ተብሎ “ለመበጥበጥ” እና “እርስ በእርስ ለማዳማት”፤ በአፋር ክልል ታጣቂዎች “በማደራጀት፣ እንዲታጠቁ ምቹ ቦታ በመፍጠር፣ በመደገፍ እና ተልዕኮ በመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ ቆይቷል” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደር ወንጅሏል። በአፋር ክልል “ሀራ መሬት” የሚል መጠሪያ በሰጡት ቦታ ላይ የሚገኙት እነዚሁ ታጣቂዎች ካለፈው ዓመት ወዲህ ተደጋጋሚ “ትንኮሳዎች” ሲፈጽሙ መቆየታቸውን መግለጫው ከስሷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው በከነባ እና አብዓላ አቅጣጫ በዚህ ዓመት በታጣቂዎቹ ተፈጽመዋል ያላቸውን ትንኮሳዎች ነው። ታጣቂዎቹ በዚህ ሳምንትም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በደቡብ ትግራይ ራያ አዘቦ እና ራያ ጨርጨር ከህዝብ እና ከባለሀብቱ ጋር የነበረውን “የልማት ውይይት” ለማደናቀፍ የሚያስችሉ ተግባራትን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን በመግለጫው አንስቷል።
ታጣቂዎቹ እነዚህን ተግባራት ይፈጽሙ የነበረው ከአፋር ክልል መጋሌ ወረዳ፣ ቶንሳ ቀበሌ በመነሳት እንደነበርም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ጠቁሟል። የአፋር ክልል መንግስት ከትላንት በስቲያ ምሽት ባወጣው መግለጫ “በህወሓት ቡድን” ጥቃት እንደተፈጸመበት የገለጸው ስፍራም ይኸው የቶንሳ ቀበሌ ነው።
ክልሉ በዚሁ መግለጫው፤ “ጠብ ጫሪ” ያለው የህወሓት ቡድን የአፋር ክልልን ወሰን ተሻግሮ በመግባት በቶንሳ ቀበሌ በሚገኙ ወረዓ እና ሚልኪ በተባሉ ቦታዎች ላይ “በንጹሃን አርብቶ አደሮች” ላይ “የከባድ መሳሪያ ተኩስ” መክፈቱን ገልጾ ነበር። የአፋር ክልል መንግስት በኮሚኒኬሽን ቢሮው አማካኝነት ያወጣውን ይህን መግለጫ “መሰረት ቢስ” ሲል ያጣጣለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ “የተረገጠ የአፋር ወሰን የለም” ሲል ጉዳዩን አስተባብሏል።
የትላንት በስቲያው መግለጫ “ችግር እየፈጠረ ያለው” አካል “መልሶ ከሳሽ በመሆን” ያወጣው እንደሆነም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል። በትግራይ በኩል የሚፈጠር “ሁከትም” ይሁን “አለመረጋጋት” እንዲኖር “በፍጹም አንፈልግም” ሲልም አስተዳደሩ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።
ድርጊቱ “ለሁለቱ ህዝቦች ሰላማዊና ታሪካዊ ወንድማማችነት እና ጉርብትና የሚመጥን አይደለም” ያለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ “የትግራይን ህዝብ ለመጉዳት የታቀደ እኩይ ተግባር መሆኑ ግልጽ ነው” ሲልም አክሏል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ቢልም፤ የአፋር ክልል መንግስት ግን “የሽብር ተግባር” ፈጽሞብኛል ያለው የህወሓት ቡድን “ከጥፋቱ የማይማር” እና “ጠብ ጫሪ” ሲል ኮንኖታል።
የክልሉ መንግስት ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫው፤ በአፋር ክልል የተፈጸመው ጥቃት የፕሪቶሪያ ስምምነትን “በግጭት አዋጅ በግልጽ ያፈረሰ” መሆኑንም ገልጾ ነበር። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት “ሳይውል ሳያድር” እንዲፈጸም በትላንቱ መግለጫው ጠይቋል።

በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት ሲካሄድ የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቋጭ ያደረገው ስምምነት በህወሓት እና በፌደራል መንግስት ተወካዮች መካከል በደቡብ አፍሪካዊቷ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመው ጥቅምት 23፤ 2015 ነበር። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትላንቱ መግለጫው፤ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት “በአግባቡ እንዲፈጸም አላስቻለም” ሲል የፌደራል መንግስትን ወቅሷል።
“የፌደራል መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በአግባቡ እንዲፈጸም አለማድረጉ፤ ሰላማዊ ሂደቱን እና መተማመንን ከመጉዳት ባሻገር የህዝብ መከራ እና ስቃይ እንዲቀጥል የሚያደርግ፣ በውጤቱም ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ ትግልን የሚያውክ መሆኑ ግልጽ ነው” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። የስምምነቱ አለመፈጸም፤ “የኢትዮጵያ እና የአካባቢውን ሰላም የሚያውክ” እንዲሁም “ያልተፈለገ ዳግም ጥፋት የሚያስከትል የውድመት መንገድ ነው” ሲልም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው አሳስቧል።
በትግራይ ክልል ያለውን ችግር እንደ እድል በመጠቀም “ውስጣዊ ችግሮች እንዲወሳሰቡ” እና “ትግራይ ዳግም የጦርነት አውድማ እንድትሆን”በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንዳሉም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ጠቁሟል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ትግራይን በጉልበት ለማዳከም የሚደረግ” ያለው እንቅስቃሴ እንዲቆም እና ውስጣዊ ችግሮችን ለመፍታት “በሰከነ መንገድ” ወደ ውይይት በመግባት መፍትሄ እንዲመጣ” ጥሪ አስተላልፏል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚሁ መግለጫው “በኃይል እና ህይወት በመገበር የሚለወጥ ሁኔታ እንደማይኖር” ገልጾ፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሳይውል ሳያድር ለመፈጸም እና ከፌደራል መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጧል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ህገመንግስታዊ” ሲል የጠራውን “የትግራይ ክልል ወሰን” እንዲረጋገጥ እና የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ዋስትናቸው ተጠብቆላቸው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም በመግለጫው ጠይቋል።
በአፋር ክልል ባለፈው ሰኞ ምሽት በተፈጸመው ጥቃት፤ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የአይን እማኞች እና ባለስልጣናት በትላንትናው ዕለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በጥቃቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ከሁለት ሺህ በላይ መሆናቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































