የዕጩዎች ምዝገባ የሚከናወነው ከጥር 1 ጀምሮ ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 ሆኖ መጽደቁን አስታወቀ። ቦርዱ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ባደረገው የጸደቀ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ፤ የምርጫ ውጤት በቦርዱ ደረጃ ይፋ የሚደረገው ሰኔ 4 ቀን እንደሆነ ገልጿል።

ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 30፤ 2018 ይፋ የተደረገው የጊዜ ሰሌዳ፤ በረቂቅ ደረጃ ከነበረው የጊዜ ሽግሽግ ተደርጎበታል። ምርጫ ቦርድ የመጪውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አዘጋጅቶ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲወያዩበት ያቀረበው ጥቅምት 10፤ 2018 ነበር። 

ቦርዱ በዚሁ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ጋር በጥቅምት ወር አጋማሽ ተመሳሳይ ውይይት ማድረጉም አይዘነጋም። ምርጫ ቦርድ ይህንኑ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ በመጠቀም የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችን ሲያከናውን ቢቆይም፤ እስከ ዛሬ ድረስ ይፋዊ የምርጫ ሂደት ዝርዝሮችን ሳያሳውቅ ቆይቷል።    

በይፋዊ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት በመጪው ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ምዝገባው የሚከናወነው ከጥር 1 እስከ የካቲት 1 ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይሆናል። የምርጫ ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ጊዜ ከጥር 1 ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 እንደሚቆይም በጊዜ ሰሌዳው ላይ ሰፍሯል። 

እንደ ዕጩዎች ምዝገባ ሁሉ አንድ ወር ጊዜ የተሰጠው የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 እንደሆነ ምርጫ ቦርድ አመልክቷል። በቴክኖሎጂ በመታገዝ ራሳቸውን ለሚመዘግቡ (self registration) መራጮች በአንጻሩ ሁለት ወር የተጠጋ ጊዜ ተመድቦላቸዋል። በዚህ ሂደት የሚሳተፉ መራጮች የሚመዘገቡት ከጥር 15 እስከ መጋቢት 7 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

መራጮች ሰኞ ግንቦት 24 ድምጻቸው ከሰጡ በኋላ ውጤቱን በምርጫ ጣቢያ ደረጃ በማግስቱ መመልከት እንደሚችሉ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ተመልክቷል። በምርጫ ክልል ደረጃ ጊዜያዊ ውጤት የሚገለጸው፤ ከድምጽ መስጪያው ማግስት ጀምሮ እስከ ግንቦት 29 ድረስ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት እንደሆነ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ተቀምጧል። 

የምርጫ ክልሎች ውጤቶችን ለምርጫ ቦርድ የሚያስረክቡት ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 1 ድረስ ባሉት ጊዜያት እንደሚሆንም በይፋዊ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተገልጿል። ምርጫ ቦርድ ውጤቶችን የማረጋገጥ ስራዎችን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2 ባሉት ቀናት ካከናወነ በኋላ ይፋዊ የምርጫ ውጤቱን ሐሙስ ሰኔ 4፤ 2018 ይገልጻል ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]