በትግራይ ህፃፅ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር “ከጊዜ ወደ ጊዜ” እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

በትግራይ ክልል ህፃፅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተጥልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ “ረሃብ” እና “ረሃብ ባስከተለው በሽታ” ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር “ከጊዜ ወደ ጊዜ” እየጨመረ መምጣቱን የተፈናቃዮቹን ጉዳይ የሚከታተሉ አንድ የክልሉ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ህወሓት፣ ስምረት እና ኢሕአፓ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዛሬው ዕለት በየፊናቸው ባወጧቸው መግለጫዎች፤ በህፃፅ ለሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የኤርትራ ስደተኞችን ለማስተናገድ በ2005 ዓ.ም የተቋቋመው ህፃፅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፤ በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ አስገደ ወረዳ የሚገኝ ነው። የስደተኞች መጠለያ ጣቢያው በትግራይ ክልል ጦርነት ወቅት በደረሰበት ጉዳት፤ በውስጡ ተጠልለው የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ስፍራውን ጥለው ወደ ሌሎች ቦታዎች ሸሽተዋል። 

ለሁለት ዓመት የዘለቀው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገ የግጭት ማቆም ስምምነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. መቆሙን ተከትሎ፤ የህፃፅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከምዕራብ ትግራይ ዞን የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። በህፃፅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከ14 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጥልለው እንደሚገኙ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የምዕራብ ትግራይ ዞንን እንዲያስተዳድሩ የሾማቸው አቶ ግደይ አዘናው ገልጸዋል። 

የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ግደይ፤ ከ2015 ዓ.ም. ወዲህ በህፃፅ መጠለያ ጣቢያ “ረሃብ” እና “ረሃብ ባስከተለው በሽታ” ከ330 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣቢያ የቆዩበት ጊዜ “እየጨመረ” በመምጣቱ፤ ችግሩ እየተባባሰ እና በሽታ የመቋቋም አቅማቸው “እየተዳከመ” መሄዱንም አስረድተዋል።

ለአንድ ተፈናቃይ በወር የሚሰጠው 15 ኪሎ ማሽላ መሆኑን የገለጹት አቶ ግደይ፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሰጠው ይህ የምግብ ድጋፍ “በቂ አለመሆኑን” አመልክተዋል። ተፈናቃዮች ከሚያገኙት እርዳታ ላይ ቀንሰው በመሸጥ ሌሎች የምግብ ግብዓቶችን መሸመት “የማይፈቀድላቸው” መሆኑ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል።

መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚመጣው እርዳታ የጥራት ችግር ያለበት እና አንዳንዱ አካባቢ “ለምግብነት የሚውል እንዳልሆነ” አቶ ግደይ ይገልጻሉ። “ከዚህ ውጭ ዘይት ብቻ ነው የሚሰጠው። ጨው የለውም። በርበሬ የለውም። ሌላ ነገር የለም” የሚሉት የምዕራብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፤ በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮች ህይወት እያለፈ የሚገኘው “ከረሃብ” በተጨማሪ “በበሽታ” ሳቢያ እንደሆነ ይናገራሉ። 

“የበሽታ ጉዳይ አለ። ህዝቡ በደም ብዛት፣ በስኳር እና ሌሎች በእድሜ መግፋት የሚመጡ በሽታዎች በብዛት እየተጠቃ ነው። አምስት ዓመት ሙሉ በኬንዳ ነው ሚኖረው። አምስት ዓመት ሙሉ ተለዋጭ ምግብ አያገኝም። አምስት ዓመት ሙሉ ጸሀይ በላዩ ላይ ነው። ተጨማሪ በሽታዎችም አሉ” ሲሉ አቶ ግደይ የችግሩን ሁኔታ አብራርተዋል።

“በረሀብ እና በበሽታ ምክንያትም የሚሞት ሰው” በሌሎች የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎችም “መኖሩን” የሚገልጹት አቶ ግደይ፣ የህፃፅ መጠለያ ጣቢያ ግን “የከፋ” እንደሆነ ጠቁመዋል። ለዚህም ምክንያቱ የህፃፅ የተፈናቃዮች መጠለያ የሚገኝበት ስፍራ ቆላማ አካባቢ በመሆኑ፤ ሞቃታማው የአየር ጸባይ ከምግብ እጥረት ጋራ ተዳምሮ ተፈናቃዮችን “ይበልጥ ለበሽታ ተጋላጭ ስለሚያደርጋቸው ነው” ይላሉ። 

በህጻጽ የተፈናቃዮች መጠለያ የሟቾች ቁጥር “ከጊዜ ወደ ጊዜ” እየጨመረ መምጣቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት የምዕራብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፤ ለተፈናቃዮች የሚሆን ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት “ዞኑ” ከባለሀብቶች ድጋፍ እያሰባሰበ መሆኑን አመልክተዋል። በህፃፅ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሁኔታን በተመለከተ በዛሬው ዕለት በየፊናቸው መግለጫ ያወጡ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የአስቸኳይ ድጋፍ አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ህጋዊ ዕውቅናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘበት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 13፤ 2018 ባወጣው መግለጫ፤ በሁሉም የተፈናቃዮች መጠለያ ማዕከላት “እየቀነሰ” የሄደው ሰብዓዊ እርዳታ፤ “ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ” መፍጠሩን አመልክቷል። የትግራይ ሰብዓዊ ቀውስ “እጅግ ወደከፋ ደረጃ ተሸጋግሯል” ያለው ህወሓት፤ ተፈናቃዩ ህዝብ “በየቀኑ በረሃብና በበሽታ እየሞተ ነው” ሲል የጉዳዩን አሳሳቢነት በመግለጫው አስታውቋል። 

የእዚህ ቀውስ አንዱ ማሳያ የሆነው በህፃፅ የተፈናቃዮች መጠለያ ማዕከል “ከባድ ረሃብ ውስጥ መግባቱ” እንደሆነ የጠቆመው ህወሓት፤ በዚህም “የወገኖቻችንን ህይወት እያጣን ነው” ሲል ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻው አሳስቧል። በህፃፅ መጠለያ ማዕከል የሚገኙት ቀሪ ተፈናቃዮች “እጅግ አሳሳቢና ከባድ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ” ያለው ፓርቲው፤ ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ እንዲጨምር ጥሪ አቅርቧል። 

ለሰብዓዊ ቀውሱ መፈጠር የኢትዮጵያን መንግሥት በመግለጫው ተጠያቂ ያደረገው ህወሓት፤ በትግራይ ላይ የሚፈጸም ነው ያለውን “የዘር ማጥፋት” ከዚህ በላይ “መታገስ እንደማይቻል” አስጠንቅቋል። ይህንንም “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘበው እንደሚገባ” ፓርቲው በመግለጫው አስገንዝቧል።

የህፃፅ የተፈናቃዮችን መጠለያ ሁኔታን በተመለከተ መግለጫ ያወጣው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) በአንጻሩ ለችግሩ መፈጠር ዋነኛ ተጠያቂ ያደረገው ህወሓትን ነው። በቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ስምረት፤ በህፃፅ ለሚገኙ ለተፈናቃዮች የአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። 

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በተመሳሳይ ተፈናቃዮች በአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው እና ጉዳያቸው በዘላቂነት እንዲፈታ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። “ከጦርነት የተረፉ ንጹሀን በረሃብ እየተገረፉ መሆኑ ትልቅ የሰብዓዊነት ልሽቀት ነው” ያለው ኢሕአፓ፤ ለተፈናቃዮች የሚደረግ ማንኛውም ድጋፍ “እርዳታ ሳይሆን የዜግነት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል ሲል ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)