በጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ላይ ግድያ መፈጸሙን ተከትሎ፤ በከተማይቱ ከትላንት ማክሰኞ ረፋድ ጀምሮ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በከተማይቱ የተለያዩ አካባቢዎች ትላንት እና ዛሬ የመሳሪያ ተኩስ እየተሰማ እንደሚገኝም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ለከተማይቱ አለመረጋጋት መንስኤ የሆነው የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ኡሞድ ኡጁሉ ግድያ የተፈጸመው ትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 7፤ 2018 ከቀኑ አራት ሰዓት ገደማ እንደሆነ የቅርብ ጓደኛቸው ተናግረዋል። የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ኡጉላ ኡጁሉ ግድያውን መፈጸሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም፤ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።
ከዚህ ክስተት በኋላ በጋምቤላ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የመሳሪያ ተኩስ እየተሰማ እንደሚገኝም የተገደሉት የፖሊስ አዛዥ የቅርብ ጓደኛ ተናግረዋል። ግለሰቡ ተኩስ ከሚሰማበት አካባቢ ስላለው ሁኔታ እና ምን አይነት ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ እንዳልቻሉ ቢገልጹም፤ ዛሬ ቀትር ላይ ወደ ከተማው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በሄዱበት ወቅት “የሞቱ እና የተጎዱ ሰዎችን” እንደተመለከቱ የአይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ተጎጂዎችን ፎቶ ማንሳት በመከልከሉ በአጠቃላይ የተጎዱ ሰዎች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ እንዳልቻሉ ግለሰቡ አመልክተዋል። የተገደሉትን የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ቤተሰቦችን ለማስተዛዘን ከክልሉ ምክር ቤት አቅራቢያ በሚገኘው የሟች መኖሪያ ቤት የነበሩት ግለሰቡ፤ በስፍራው ሆነው የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማቸው እና በአካባቢው “የሰዎች እንቅስቃሴ እንደሌለ” አክለዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሁለት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች፤ ትላንት እና ዛሬ በከተማይቱ የተኩስ እንደሚሰማ እና መደበኛ እንቅስቃሴ መቆሙን አረጋግጠዋል። በትላንትናው ዕለት የነበረው ተኩስ የቆመው፤ ማታ ሶስት ሰዓት ገደማ ከዘነበው ዝናብ በኋላ እንደነበር አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ተናግረዋል።
ሆኖም ዛሬ ጠዋት ለሶስት ሰዓት ሩብ ጉዳይ አካባቢ በድጋሚ ተኩሱ መጀመሩን እና ከሰዓቱንም መቀጠሉን ነዋሪዋ ገልጸዋል። የተኩሱ ድምጽ የሚመጣው ከጋምቤላ ከተማ ወደ ላሬ ወረዳ እና አቦል ከተማ መሄጃ መንገዶች በኩል እንደሆነም አብራርተዋል።

በከተማይቱ የሚሰማው ተኩስ ዛሬ ጠዋት ሲያገረሽ ከቤታቸው ወጥተው መንገድ ላይ እንደነበሩ የገለጹት ነዋሪዋ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በመንገድ ላይ ሲሯሯጡ ተመልክቼያለሁ ብለዋል። በተኩስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ዛሬ ከሰዓት መስማታቸውንም አክለዋል።
“ያለንት ሁኔታ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ነው። ትላንት በስንት መከራ ነው ልጆቻችንን ይዘን ወደ ቤት የገባነው” ሲሉ እኚሁ ነዋሪ የከተማዋን ድባብ ገልጸዋል። በከተማው ዛሬም ትምህርት ቤት ለመሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን፤ እርሳቸውም በስራ ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸውን አክለው ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ህዳር 30 ተፈጽሞ በነበረ የሽጉጥ ጥቃት ምክንያት በከተማይቱ ተመሳሳይ አለመረጋጋት ተከስቶ ነበር። ይህንን ተከትሎ የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር፤ በተሽከርካሪዎች እና በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት እላፊ ማወጁ ይታወሳል።
በከተማይቱ ያለውን “ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ” በምክንያትነት የጠቀሰው የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር፤ ከጸጥታ አካላት ውጭ ያሉ ማንኛውም ተሽከርካሪዎች እና ሰዎች ከምሽት አንድ ሰዓት ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ጥሎ ነበር። የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ኡጉላ ኡጁሉ ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫ፤ በጋምቤላ ከተማ “አንዳንድ” አካባቢዎች የተፈጠሩ መጠነኛ አለመረጋጋቶች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሳቸውን አስታውቀው ነበር።
ኮሚሽነሩ በዚሁ መግለጫቸው፤ በጋምቤላ ከተማ እንዲሁም በኢታንግ፣ ጋምቤላ እና ላሬ ወረዳዎች ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸው ነበር። አቶ ኡጉላ መግለጫውን ከሰጡ ከአንድ ቀን በኋላ የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ግድያ፤ በከተማይቱ ያለውን ውጥረት አባብሶታል።
በጋምቤላ ከተማ በከፊል ሥራ ጀምረው የነበሩት የንግድ ተቋማት እና ባንኮች ከትላንት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መዘጋታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በጋምቤላ ከተማ ስለተፈጸመው ግድያ እና ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ኮሚሽነር ኡጉላ፤ “ካለው ሁኔታ አንጻር ስለጉዳዩ ለማውራት ጊዜ የለኝም” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































