ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም “በየዋህነት፣ በተላላ፣ በአጭር ጊዜ ድል” አሳልፋ እንደማትሰጥ፤ የተሰጠ ካለም “ማወራረዷን እንደማትተው” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቀጣዩ ዐቢይ ተግባር” የኢትዮጵያን “ስትራቴጂክ ፍላጎት” እና “ብሔራዊ ጥቅም” ማረጋገጥ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢፌዲሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ምስረታን አስመልክቶ፤ ቢሾፍቱ በሚገኘው የተቋሙ ዋና ቅጽር ግቢ በተዘጋጀ ክብረ በዓል ላይ ዛሬ ቅዳሜ ጥር 16፤ 2018 ባደረጉት ንግግር ነው። የኢፌዲሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት አብይ በዚሁ ንግግራቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ላለፉት ዘጠኝ አስርት ዓመታት “በብዙ ከፍታ”፣ “በብዙ ዝቅታ” ውስጥ ማለፉን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልን “ስመጥር” እና “ታላቅ” ሲሉ ያሞካሹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተቋሙ አሁን ያለበት ቁመና በየዘመናቱ የነበሩ መንግስታት የሰሯቸው “ድምር ስራዎች ውጤት” እንደሆነ ገልጸዋል። አየር ኃይሉ አሁን ያለበት ደረጃ፤ “ላለፉት 90 ዓመታት ከነበረበት “ከፍ ያለ” እና “የላቀ ብቃት የያዘበት ጊዜ” እንደሆነ “በድፍረት መናገር” እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

የእዚህን ወታደራዊ ተቋም አቅም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት “በእጥፍ ደረጃ” ለማሳደግ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ግልጽ እቅድ”፣ “በጀት” እና “ምንጭ” ለይቶ ከዋና ዋና አምራቾች ጋር “በትብብር” ስራ የጀመረ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። አየር ኃይሉ በአሁኑ ወቅት “የአራተኛው ትውልድ” የመዋጋት አቅም መገንባቱን የገለጹት አብይ፤ በ2030 “ወደ አምስተኛ ትውልድ” የሚሸጋገር እና በቁጥር ደረጃም አሁን ካለው “በእጥፍ” የሚጨምር መሆኑን ተናግረዋል።
“በአየር ኃይል መብቃት፣ ማሳደግ የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት በስጋ እና በአጥንት ድል ማስመዝገብ ያደረ፣ የቀረ ስርዓት ስለሆነ [ነው]። በተኩስ አቅም፣ ኢላማን በትክክል በመምታት (precision)፤ ብዙ ምሽጎች ማፍረስ እና ውጊያን ማሳጠር ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫን እንከተላለን” ብለዋል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ።
ኢትዮጵያ ለወዳጆቿ “በሯን እየከፈተች” እንደምትገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ለጠላቶቿ ግን በሯ “በቅጡ መዘጋቱን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ” አጽንኦት ሰጥተዋል። አብይ “ጠላቶቻችን” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፤ ባለፉት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያን “አቅም ለማዳከም፣ “ስትራቴጂክ ጥቅሞቿን ለማደናቀፍ” እና “ጥቅሞቿን ለማጋራት” በብዙ “መድከማቸውን” እና “መስራታቸውን” አመልክተዋል።

“ጠላቶችንን በሚመለከት የኢትዮጵያን ክብር፣ የኢትዮጵያን አንድነት፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ተኝተን የማናድር መሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ እወዳለሁ” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። “ወዳጅም፣ ጠላትም አንድ እንዲገነዘብ የምፈልገው ነገር፤ ኢትዮጵያን በቅጡ፣ ኢትዮጵያን በበቂ አናውቃትም። ኢትዮጵያ ከምታውቋት ያለፈች ሀገር ናት” ሲሉም አክለዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር “ተስማምቶ፣ ተባብሮ አብሮ ማደግ ብቻ ነው የሚያዋጣው” ያሉት አብይ፤ ከዚያ ውጭ ያለው አማራጭ “ጥፋት እንደሚያስከትል” አስጠንቅቀዋል። “አንዳንዴ የምትስቱ፣ ቆማችሁ የቀራችሁ፣ ወደፊት መራመድ የምትቸገሩ፤ SU 30፣ JC 10 ወይም ከዚያ ያለፉ ቴክኖሎጂዎች ሲጠሩ ‘ይሄ ደግሞ ምንድነው ብላችሁ’ ግራ የሚገባችሁ፤ አሁንም ሚግ 21 ላይ ያላችሁ ሀገራት፤ ደጋግማችሁ እንድታስቡ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያ ትላንት ላይ የቆመች ሀገር አይደለችም” ሲሉም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ በግልጽ ላልጠቀሷቸው ሀገራት መልዕክት አስተላልፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































