መብራት አልነበረም። በተንቀሳቃሽ ስልክ መብራት ወደ ቤቷ እየመራችን እንድንገባ ጋበዘችን። ‘ሁሉን አቀፍ’ የሆነች አንድ ክፍል ቤቷ ውስጥ፣ ሰፊውን ቦታ የያዘው አልጋ ነው። የልብስ ሳጥን፣ የምግብ ማብሰያ የተወሰኑ ቁሳቁሶች፣ እድሜ የጠገበ መሆኑ የሚያስታውቅ ተካፋች አጠር ያለ መደርደሪያ እና ከላዩ ባለው የግድግዳ ማዕዘን ቁልቁል የሚወርዱ፣ ጭስ ንጣቱን ሊጋርድ በሚታገለው መጋረጃ የተሸፈኑ የቅዱሳን ሥዕላት ይታያሉ።
ወይዘሮ ውዴ ቱሉ፥ ፈገግታዋ የቤቱን በጨለማ መዋጥ ያስረሳል። ሽበት የወረረው ጸጉር ካደረገችው ሻሽ አፈትልኮ ይታያል። “የበዓል ዝግጅት እንዴት ነው?” ስትል ‘ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ ጠየቀች። የውዴ መልስ አጭር ነበረ፥ “በዓል ማክበር ትቻለኹ።”
ከመኖሪያዋ በቅርብ ርቀት የሚገኘው፤ ከየረር-በር ወደ ጎሮ በሚወስደው መንገድ የነበረው የጉሊት ስፍራ ፈርሶ ከመነሳቱ በፊት በዚያ ብዙ ደንበኛ ካላቸው ነጋዴዎች መካከል ነበረች። ጎመንን ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችን ለገበያ ታቀርባለች። በዚያን ወቅት በዓል ሲደርስ እንዲህ እንደ አሁኑ ሐሳብ አይሆንባትም ነበር።

“በፊት [የ]ጉሊት [ንግድ] በምሠራበት ሰዓት [በዓልን] ደስተኛ ሆኜ፣ ቤትም ጥሩ አድርገን ነበር የምናሳልፈው። ቤቴን አሟልቼ ከጎረቤቶቼም ጋር እጠራራለኹ። አሁን ግን ጉሊቱ ከፈረሰ በኋላ እንኳን ለበዓል ለጉሮሮ የለኝም። ጉሊቱ ከፈረሰ በኋላ እኔም በሽተኛ ሆንኹ፣ ደም ግፊት መጣ። መድኃኒት መጠቀም ጀመርኹ።” አለች። ከዚያ ወዲህ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮዋ በዓልን በተለመደው መንገድ እንድታከብር እድል አልሰጣትም።
የአንድ የ17 ዓመት ልጅ እናት የሆነችው ውዴ፣ አሁንም በጉሊት ንግድ ውስጥ ናት። በመኖሪያ ቤቷ አቅራቢያ፣ ሰፈር ውስጥ በመደብ ጎመን እና ድንች በመሸጥ ሥራ ላይ ተሰማርታለች። ሆኖም ወትሮውን የኑሮዋን ቀዳዳ ሸፍኖ ለበዓል ይተርፋት እንዳልነበር፣ አሁን ግን በዓልን ማሰብ ቅንጦት ሆኖባታል። ምን ጥራ ግራ ሠርታ ገቢ ብታመጣ፣ ከቤት ኪራይና ከእለት ቀለብ የሚያልፍ አልሆነም።
“የኑሮው ውድነትና ጫና በደንብ ተሰምቶኛል። እንደ ድሮው [ለበዓል] አላደርግም፣ ያንን የማዘጋጅበት አቅም የለኝም። የቤት ኪራይ አለብኝ፣ ከሥራዬ የማገኘው ገቢም እንደ ድሮው አይደለም” በማለት የኑሮ ጫና እና በዓል አብረው የሚሄዱ ጉዳዮች እንዳልሆኑላት ትናገራለች።

ምስጋና ለጎረቤቶቿ ይግባና የበዓል ደስታን የሚያጋሯት ጎረቤቶች እንዳሏት ትጠቅሳለች። “በዓል ሲሆን ጎረቤቶቼ ይጠሩኛል፣ ከእነሱ ጋር አከብራለኹ። እንጂ እኔ የማዘጋጀው ነገር የለም” ስትል በአዲስ አበባ ያለው የኑሮ ውድነት ጫና እንደ እርሷ ባሉ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ታስረዳለች።
በአዲስ አበባ ከተማ የበርካታ ሸቀጣ ሸቀጦች እና የበዓል ምግብ ግብዓት የሆኑ ምርቶች ዋጋ መጨመር፣ ብዙ ቤተሰቦች በዓሉን እንዲሁ ‘ቀለል አድርገው’ እንዲያሳልፉ አስገድዷቸዋል። እንዲህ ያለው የዋጋ መጨመር የበዓሉን መንፈሳዊ እሴት ባይቀንሰውም፣ የተለመደውን ባህል ቀመስ አከባበር መቀየሩን ግን መታዘብ ይቻላል።
በበዓል ወቅት በመንግሥታዊና በግል ተቋማት ከሚደረጉ የማዕድ ማጋራት የሚቋደሱ ዜጎች ጥቂት አይደሉም። በዚህ ዓመትም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በማዕድ ማጋራት ከ 300 ሺህ በላይ አቅመ ደካማ ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸው በከተማ አስተዳደሩ ተገልጿል።

ከዚህ በከተማ አስተዳደር እና በተቋም ደረጃ ከሚደረግ ድጋፍ በተጓዳኝ፣ የተለያዩ ግለሰቦች በግልም በጋራም በበዓላት ቀን የተቸገሩ ዜጎችን የመጎብኘትና በቻሉት አቅም የማገዝ ልምድ አላቸው። ሀና ኃይሉ እንዲህ ካለው ድጋፍ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ናት።
ወደ ጃክሮስ መብራት ኃይል አካባቢ ነው መኖሪያዋ። ወጣት ናት፣ ሠላሳዎቹን እድሜ ጨርሳ አላጠናቀቀችም። ፊቷ ‘ሞላ ያለ’ የሚባል ዓይነት ይሁን እንጂ፣ ገጽታዋ የውስጧን አንዳች ድካም ይናገራል። ፊቷን ያበለዘው “ላለብኝ ሕመም የምወስደው መድኃኒት ተጽእኖ ነው” ትላለች።
ስለ በዓል ስናነሳባት “በዓልን ደስ ብሎኝ ውዬ አላውቅም” በማለት ወጓን ትቀጥላለች። ይህ ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ግን አታስታውስም። ብቻ ከ13 ዓመት ገደማ በፊት ኑሮዋን በቋሚነት በአዲስ አበባ በመሠረተችበት ወቅት፤ ጎመን ነግዳና በሰው ቤት የታዘዘችውን ሠርታ የእለት ጉርሷንም ሆነ በዓል ማሳለፊያ ገንዘብ አታጣም ነበር። “ያኔ ኑሮውም ጥሩ ነበር” ትላለች።

“በፊት በልብስ አጠባም ይሁን ያገኘሁትን ሠርቼ ዓመት በዓልን ጥሩ አሳልፍ ነበር። ያኔ ኑሮም ደኅና ነበር። ዘይትም፣ ዱቄትም ከሸማች በቅናሽ አገኛለኹ። ጎመን ንግድም ጥሩ ነበር። አሁን ግን ሁሉም ተወደደ” ስትል በሥራ ላይ እያለች ጀምሮ የኑሮው ጫና በተለይ በበዓላት ሰሞን ክብደቱን እንደጨመረ ትጠቅሳለች።
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በገጠማት የልብ ሕመም ምክንያት፣ እንደ ቀደመው ጊዜ ወዲያ ወዲህ ብላ ልብስ አጠባም ይሁን ሌላ ሥራ መሥራት አልሆነላትም። ሰውነቷም ለዚያ አልታዘዝ አላት። እናም በተለያየ መልክ በሚገኝ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ሆነች። ድጋፉም ቢሆን ግን ከካቻምና አምና፣ ከአምና ደግሞ ዘንድሮ ልዩነት እንዳለው ታነሳለች።
ከተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች የምታገኘው እርዳታ መጠኑና ዓይነቱ እየተለወጠ፣ እየቀነሰም መሄዱን ታብራራለች። “ከአንድ ዓመት በፊት ለበዓል የሚሆን ዶሮ፣ እንቁላል፣ ዱቄትም 25 ኪሎ አካባቢ አገኝ ነበር። አሁን ከዚያ ቀንሷል። በድጋፍ የማገኘውን ዱቄትና ዘይት ቆጥቤ ለየእለት ምግቤ ነው የማውለው” ስትል ታስረዳለች።

በዚህ ሁሉ መካከል ነው እንግዲህ፣ በዓል ሲመጣ ከደስታ ይልቅ መከፋት የሚቀድማት። እንደውም “ቡና ጠጭ” ብለው ለበዓል የሚጠሯትን ጎረቤቶችና በዓል ተኮር ድጋፎች የማታገኝ ቢሆን ኖሮ፤ የበዓል ዕለትን ጣዕም ፈጽሞ ሳታገኝ ትቀር እንደነበርም ትናገራለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































