በግጭት ውስጥ የሰነበተው የጋምቤላ ክልል ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል?

በጋምቤላ ክልል አንጻራዊ መረጋጋት መስፈኑን እና ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው “እየተመለሱ መሆናቸውን” የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው አካባቢያቸው ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ቢሆንም ትምህርት ቤቶች አሁንም ዝግ መሆናቸውን እና አልፎ አልፎ ምሽት ላይ የተኩስ ድምጾች እንደሚሰሙ ተናግረዋል።

የክልሉ ዋና መቀመጫ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ ህዳር 28፤ 2018 በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን እና ሌላ ግለሰብ መቁሰሉን ተከትሎ፤ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በግጭቶች ውስጥ ቆይተዋል። ግጭቱ ይበልጥ የተባባሰው፤ የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ኡሞድ ኡጁሉ ከሁለት ሳምንት በፊት ማክሰኞ ታህሳስ 7 ከተገደሉ በኋላ ነበር።

የጋምቤላ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ፤ አሁን በክልሉ ያለው ሁኔታ “ተረጋግቷል” ብለዋል። በክልሉ በሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ምክንያት ነዋሪዎች ወደ ስራ ገበታቸው “እየተመለሱ” መሆናቸውንም ወ/ሮ አለሚቱ አክለዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

እንደ ሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎቹ ሁሉ የጋምቤላ ከተማ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኗን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሯ፤ ለዚህም በከተማይቱ የሚገኙ የንግድ ሱቆች እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት “በሙሉ” ወደ ስራ በመግባት ላይ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። 

አንዲት የከተማይቱ ነዋሪ በከተማይቱ ያሉ የንግድ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ቀስ ቀስ እያሉ አሁን በሰፊው መደበኛ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል። ይሁንና የግል ትምህርት ቤቶች በከፊል ስራ መጀመራቸውን እና የመንግሥቶቹ ግን የመማር ማስተማር ስራቸውን እንዳልጀመሩ አስረድተዋል። 

ሌላኛው የከተማይቱ ነዋሪም ትምህርት ቤቶች አሁንም በአብዛኛው “ዝግ መሆናቸውን” አረጋግጠዋል። “ባሮ ማዶ” በሚባል የጋምቤላ ከተማ አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ባለፈው ሳምንት ትምህርት መጀመሩን የገለጹት እኚሁ ነዋሪ፤ ከዚያ በኋላ “ወጣ ገባ ያለ” የመማር ማስተማር ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።

ፎቶ፦ የጋምቤላ ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

ነዋሪዎቹ ያነሱትን የትምህርት ቤቶች ጉዳይ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለተፈናቀሉ ሰዎች ማረፊያ በመሆናቸው ወደ ማስተማር አለመመለሳቸውን ገልጸዋል። በክልሉ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለው በጋምቤላ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች፤ ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንደ ጀመሩ ርዕሰ መስተዳድሯ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ፤ ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በጋምቤላ ክልል “ግጭት” እና “የጸጥታ መደፍረስ” የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ጋምቤላ ከተማ፣ ጋምቤላ ወረዳ (አቦል ከተማ) እና ኢታንግ ልዩ ወረዳ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። ከአቦል ከተማ እና ከኢታንግ ልዩ ወረዳ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፤ በጋምቤላ ከተማ በሚገኘው የኢሌይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተጠልለው ቆይተዋል።

ከእነዚህ አካባቢዎች ተፈናቅለው በትምህርት ቤቱ የተጠለሉ ሰዎች ቁጥር 2,500 ገደማ መድረሱንም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብርሃም ኦታውም ባለፈው ሳምንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸው ነበር። ተፈናቃዮች ወደ የአካባቢያቸው በመመለስ ላይ ላይ መሆኑን በዛሬው ዕለት ያረጋገጡት ርዕሰ መምህሩ፤ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቱ የቀሩት ተፈናቃዮች 500 መሆናቸውን አመልክተዋል።

ፎቶ፦ የጋምቤላ ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

እነዚህ ተፈናቃዮች በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ “ያለ ፍራሽና መሰል አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተጠልለው” እንደሚገኙ የገለጹት አቶ አብርሃም፤ ከህብረተሰቡ እና ከሃይማኖት ተቋማት የምግብ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አሁንም ተጠልለው ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑት ከኢታንግ ልዩ ወረዳ የመጡ መሆናቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መምህሩ፤ ተፈናቃዮቹ “ቤታቸው በመቃጠሉ” ምክንያት ወደ ቀዬአቸው መመለስ አለመቻላቸውን አስረድተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በትምህርት ቤቱ የሚገኙ አንድ ተፈናቃይ፤ ንብረታቸው “በሙሉ በመዘረፉ” ምክንያት ወደ ቀያቸው እንዳልተመለሱ ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ተፈናቅለው ከነበሩ የክልሉ ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን መስክረዋል።

ከተፈናቃዮች መካከል “የሚቀር ካለ በራሱ ጊዜ የቆየ” እንደሆነ የሚገልጹት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፤ “አንዳንዶቹ ቤተሰብ ቤት ያሉ በመሆናቸው” እንጂ መመለስ የሚችሉበት የሰላም ድባብ በክልሉ መፈጠሩን በአጽንዖት ገልጸዋል። የአቦል ከተማ ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መመለሳቸውን እና ከኢታንግ ልዩ ወረዳ የተፈናቀሉትም በመመለስ ላይ መሆናቸውን አክለዋል። 

ፎቶ፦ የጋምቤላ ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

በኢታንግ ልዩ ወረዳ በአሁኑ ወቅት “ሰላማዊ ሁኔታ እንዳለ” የገለጹት ወ/ሮ አለሚቱ፤ ሆኖም “በራሳቸው ምክንያት ያልተመለሱ አሉ” ሲሉ አሁንም በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተጠለሉ ተፈናቃዮች እንዳሉ አመልክተዋል። ተፈናቃዮች ተመልሰው ሲያልቁ፤ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ አመቺ ለማድረግ የማጽዳት እና የማሰናዳት ስራ ተሰርቶ ትምህርት ከሰሞኑ እንደሚጀመርም ጠቁመዋል። 

ትምህርትን ጨምሮ እስከታች ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟላ መልኩ ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል “አመራሩን ሰብስበን እያነጋገርን ነው” ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሯ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በመንግስት ተቋም ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ አንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ እርሳቸው የሚሰሩበት ተቋም ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ሆኖም ሰራተኞች በብዛት እየገቡ እንዳልሆነ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። 

የጋምቤላ ክልል የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ በዛሬው ዕለት ለ53 የክልሉ ተቋማት በላከው ደብዳቤ፤ ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ “ጥብቅ ቁጥጥር” እንዲያደርጉ አሳስቧል። ለጸጥታ ችግር ተጋላጭ በሆነ ቦታ የሚገኙ ተቋማት ሰራተኞች፤ ያለ ስጋት ገብተው እንዲወጡ “ጥበቃ እንደሚደረግላቸው” የክልሉ መንግስት መልዕክት ማስተላለፉን ቢሮው በደብዳቤው ጠቅሷል።

የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ አጠቃላይ የክልሉን “ሰላም እያስጠበቁ” የሚገኙት በዋናነት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሆኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። አንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪም፤ በከተማይቱ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ ፖሊስ አባላት በብዛት እንደሚታዩ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

በጋምቤላ ክልል አሁን ካለው አንጻራዊ መረጋጋት አንጻር፤ በክልሉ በተጣለው የሰዓት እላፊ ላይ የሚደረግ ለውጥ ይኖር እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ርዕሰ መስተዳድሯን ጠይቃለች። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተጣለው የምሽት ሰዓት እላፊ ገደቡ አሁንም እንዳልተነሳ የገለጹት ወ/ሮ አለሚቱ፤ በሰላሙ መደፍረስ ብቻ ሳይሆን “የህዝቦችንም ደህንነት ለመጠበቅ” የተደረገ ስለሆነ የሚነሳበት ጊዜ ገና መሆኑን አስረድተዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሯ ለዚህ በምክንያትነት የሚያነሱት፤ በተለያዩ ቦታዎች “ጸረ ሰላም ሀይሎች” መኖራቸውን ነው። “አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልጉ ሊኖሩ ስለሚችሉ በዚያ ምክንያት እንጂ ይሄን ያክል የከፋ ነገር የለም” ሲሉም አክለዋል። የጋምቤላ ክልል መንግስት የዛሬ ሁለት ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ “የክልሉ ህዝብ ሰላም መሆን እንቅልፍ የሚነሳቸው” እና “ግጭትና የሰው ሞት የሚያስደስታቸው” ያላቸውን “ኃይሎች” ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተጠያቂ ማድረጉ አይዘነጋም።

በጋምቤላ ክልል በተከሰተው “የጸጥታ ችግር ምክንያት”፤ የክልሉ መንግስት ከማክሰኞ ታህሳስ 15፤ 2018 ጀምሮ የሰዓት እላፊ መጣሉ ይታወሳል። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የሚቆየው የሰዓት እላፊ ገደብ ተግባራዊ የሚደረገው በጋምቤላ ከተማ እና “የጸጥታ ችግር ይስተዋልባቸዋል” በተባሉ አካባቢዎች በሙሉ እንደሆነ የክልሉ መንግስት በወቅቱ ገልጾ ነበር።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች፤ የሰዓት እላፊ ገደቡ ለመጣው አንጻራዊ ሰላም አስተዋጽኦ እንዳለው ያምናሉ። የእንቅስቃሴ ገደቡ ቢቀጥል እንደሚደግፉም እነዚሁ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ በከተማይቱ ምሽት ላይ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጾች እንደሚሰሙ ግን አልሸሸጉም።

በጋምቤላ ክልል ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተገናኘ ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ “አሁን ግጭቱን የማረጋጋት ስራ ነው እየሰራን ያለነው። የተያዘም ካለ የሚነገርበት ሰዓት አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቀጣይ ይወሰዳል ያሉትን “በጥናት ላይ የተመሰረተ” እርምጃ ጨምሮ ሌሎችም ጉዳዮች ወደፊት እንደሚገለጹም ተናግረዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ውይይት መጀመሩን የጠቁሙት ወ/ሮ አለሚቱ፤ ትላንትና እና ዛሬ እስከ ዞን ድረስ የዘለቀ ውይይት መካሄዱን አስታውቀዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በጸጥታው መደፍረስ ምክንያት ሸሽተው ከክልሉ የሄዱ ሰዎች እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል። “በስጋት የወጡ ሊኖሩ ይችላሉ። አሁን ወደ ክልሉ መጥተው የቢዝነስ ስራቸውን ማስቀጠል ይችላሉ። በአሁኑ ሰዓት ምንም ችግር የለም” ሲሉም ወ/ሮ አለሚቱ ማስተማመኛ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)