በጋምቤላ ከተማ ከሰኞ ጀምሮ ወደ ትምህርት የማይመለሱ ተማሪዎች ከፈተና ሊታገዱ ነው 

በጋምቤላ ከተማ ከነገ በስቲያ ሰኞ ጀምሮ በትምህርት ገበታቸው ላይ የማይገኙ ተማሪዎች፤ ለአንደኛ ወሰነ ትምህርት (ሴሚስተር) ማጠቃለያ ፈተና መቀመጥ እንደማይችሉ የከተማይቱ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስጠነቀቀ። በከተማይቱ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደታቸውን ካቋረጡ ትምህርት ቤቶች መካከል አምስቱ አሁንም ትምህርት አለመጀመራቸውን ጽህፈት ቤቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

የጋምቤላ ክልል መንግስት መቀመጫ በሆነችው የጋምቤላ ክልል 14 የመንግስት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። በከተማይቱ ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተ “የጸጥታ መደፍረስ” እና “ግጭት” ምክንያት ለአንድ ወር ያህል ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው ቆይተዋል።

የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በግጭት ውስጥ ከቆዩት ከአቦል ከተማ እና ከኢታንግ ልዩ ወረዳ የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መጠለያ ሆነው አገልግለዋል። ግጭት በነበረባቸው በእነዚህ ቦታዎች አንጻራዊ መረጋጋት መስፈኑን ተከትሎ፤ በትምህርት ቤቶች ተጥልለው የነበሩ ተፈናቃዮችም ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል።

በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻሉን ተከትሎ፤ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ከታህሳስ 27፤ 2018 ጀምሮ ወደነበረበት እንዲመለስ የክልሉ ትምህርት ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። በተመሳሳይ መልኩ በጋምቤላ ከተማ “በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም” የመማር ማስተማር ሂደቱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመለስ  መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር የከተማይቱ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኡሞድ ኡፖዲ፤ በጋምቤላ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት መልሶ እንዲጀመር ውሳኔ የተላለፈው ከሁለት ሳምንት በፊት እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህን ተከትሎም በግል ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ መጀመሩን ኃላፊው ገልጸዋል።

ሆኖም በመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አምስቱ እስካሁንም ድረስ ወደ መማር ማስተማር ሂደታቸው አለመመለሳቸውን አቶ ኡሞድ አመልክተዋል። በተቀሩት ትምህርት ቤቶችም ቢሆን የሚመጡት ተማሪዎች “ሙሉ ለሙሉ” አለመሆኑንም አክለዋል።

ከሳምንታት በፊት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በከተማይቱ ያለው ጀጀቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ዝርፊያ እንደተፈጸመበት የገለጹት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ፤ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኙት የፌዴራል ሰራዊት አባላት እንደሆኑ አስረድተዋል። በዚህ ምክንያት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በአቅራቢያው ወደሚገኘው ዊቡር ትምህርት ቤት ተዛውረው የመማር ሂደታቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑን ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ለጀጀቤ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የዝውውር ውሳኔ እንዳሳለፈ ሁሉ፤ በአንደኛ ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሽግሽግ አድርጓል። አስቀድሞ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የአንደኛ ሴሚስተር ፈተና በጋምቤላ ከተማ ይሰጥ የነበረው ከጥር 18 እስከ 22 ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ ነበር።  

ሆኖም በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመማር የማስተማር ሂደቱ በመስተጓጎሉ፤ የአንደኛ ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና መስጪያ ቀናት በአንድ ሳምንት ወደፊት እንዲገፋ መደረጉን አቶ ኡሞድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የከተማይቱ ትምህርት ጽህፈት ቤት ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎች ለፈተናው ከመቀመጣቸው በፊት ከጥር 12 እስከ 24 ባሉት ቀናት የማካካሻ ትምህርት እንዲወስዱ ውሳኔ አሳልፏል። 

የማካካሻ ትምህርቱን ያልወሰዱ ተማሪዎች “እንዳልተማሩ” እና “ለፈተናው ብቁ አይደሉም” ተብለው እንደሚቆጠሩ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ገልጸዋል። ጽህፈት ቤቱ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱ ተማሪዎችንም የአንደኛ ሴሚስተር ፈተና ከመውሰድ እንደሚያግዳቸውም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)