የፈረንጆቹ 2026 ዓመት ከገባ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የስድስት ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ሊገባደድ ጥቂት ቀናት በቀሩት የፈረንጆቹ ጥር ወራት፤ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፈር ላንዳውን ጨምሮ ጀርመን እና ቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል።
የፈረንጆቹ አዲስ ኦዓመት ከባተ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ቀዳሚ የሆኑት፤ የኦማን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ካሊፋ ቢን አሊ አል ሀርቲን ናቸው። የኦማን ጎረቤት የሆኑት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ በተመሳሳይ መልኩ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን በቀናት ልዩነት ወደ አዲስ አበባ ልከው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል።
ሁለቱ የመካከለኛው ምስራቅ ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ በተጓዙበት በተመሳሳይ ሳምንት፤ የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ አዲስ አበባ ነበሩ። ዋንግ ዪ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የሩቅ ምስራቋ የቻይና ጎረቤት ጃፓን፤ የወሩ ቀጣዩ ተረኛ ነበረች። የጃፓን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን አስከትለው ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጡት።
እንደ መካከለኛው ምስራቅ እና ምስራቅ እስያ ሀገራት ሁሉ አውሮፓውያኑም በዚህ ወር ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ብለው ነበር። ኢትዮጵያ የኖሮዌይ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪያስ ክራቪችን ካስተናገደች ከአንድ ቀን በኋላ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሐን ቫደፉልን ተቀብላለች።
በኬንያ የነበራቸውን ተመሳሳይ ጉብኝት አጠናቅቀው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ አዲስ አበባ የገቡት ቫደፉል፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ከኢትዮጵያ አቻቸው ዶ/ር ጌዲዮን ጋር ተገናኝተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ዋነኛ ትኩረት፤ ቀጠናዊ መረጋጋት እና ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች እንዲሁም ከባቢ አየርን በተመለከተ የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።

እንደ ጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬንያ እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ ጉብኝታቸው ያካተቱት የአሜሪካው ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፈር ላንዳው፤ የዛሬ የኢትዮጵያ እንግዳ ናቸው። ላንዳው ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በግብጽ ጉብኝት ነበራቸው።
ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በካይሮ በነበራቸው ቆይታ ከግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። የሁለቱ ዲፕሎማቶች ውይይት ያተኮረው፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና በጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንደሆነ ተዘግቧል።
ከላንዳው የአፍሪካ ጉዞ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት የገቡበትን ውዝግብ ለመፍታት እንደሚሹ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በስዊትዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው በተወያዩ ጊዜም ይህንኑ አስተጋብተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በዚሁ ውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለውን ውዝግብ በስምምነት ለመፍታት እንዲቻል የሁለቱን ሀገራት መሪዎች ማገናኘት እንደሚፈልጉ አስታውቀው ነበር። የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ “በቀጠናዊ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች” ላይ እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዛሬው ውሏቸው፤ አብረዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዙት የአሜሪካ ጦር የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ጋር በመሆን ቢሾፍቱ በሚገኘው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ቅጽር ግቢ የተዘጋጀውን “ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኤክስፖ” ጎብኝተዋል። ላንዳው የኢትዮጵያ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት፤ ረጅም ዓመታት ላስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ራሷ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን “በቀጣናው በጣም አስፈላጊ ኃይል ነች” ያሉት ላንዳው፤ “በቀጠናው ያሉትን አንዳንድ ግጭቶች ለመፍታት በጋራ ጠንካራ ሚና መጫወት እንችላለን ብለን እናስባለን። እዚህ ኢትዮጵያ ያለሁት፤ ሁለቱ ሀገሮቻችን ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ጠንካራ እና ይበልጥ የበለጸጉ እንዲሆኑ እንዴት በተሻለ ሁኔታ እንደምንተባበር እና አብረን ወደፊት እንደምንራመድ ከአመራራችሁ ጋር ለመወያየት ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአሜሪካው ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተገናኝተው እንደሚወያዩ መስሪያ ቤታቸው ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































