በትግራይ ክልል፣ መቐለ ከተማ፣ ዛሬ ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ የቦምብ ፍንዳታ መከሰቱን የከተማይቱ ፖሊስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። ፍንዳታው የደረሰው በትግራይ ክልል ምክር ቤት እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት መካከል ባለ ቦታ ላይ እንደሆነ የከተማይቱ ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ይህን ከማስታወቁ አስቀድሞ ክስተቱን በተመለከተ በማህበራዊ የትስስር ገጾች የተጋሩ መረጃዎች፤ የቦምብ ፍንዳታው የደረሰው በትግራይ ክልል ምክር ቤት ውስጥ እንደሆነ አመልክተው ነበር። ይህን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የመቐለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሀዱሽ ህዱግ መረጃዎቹን አስተባብለዋል።
የቦምብ ፍንዳታው የደረሰው የክልሉ ምክር ቤት እና የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤቱን ከሚለየው አስፋልት 500 ሜትር ርቆ ካለ ቦታ ላይ እንደሆነ ኮማንደር ሀዱሽ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በፍንዳታው በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የገለጹት ኮማንደሩ፤ የከተማው ፖሊስ ድርጊቱን ማን እንዳፈጸመው በማጣራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

የዛሬ ምሽቱ የቦምብ ፍንዳታ የደረሰው፤ በ2012 ዓ.ም. በተካሄደ አወዛጋቢ ምርጫ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ምክር ቤት፤ በነገው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሄድ እንደሆነ በማህበራዊ የትስስር ገጾች መረጃዎች ሲዘዋወሩ መዋሉን ተከትሎ ነው። የክልሉ ምክር ቤቱ ስብሰባ ነገ ማክሰኞ እንደሚካሄድ ቢነገርም፤ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ቀድሞ የህወሓት፣ አሁን ደግሞ የስምረት ፓርቲ አባል የሆኑ የምክር ቤት አባላት ግን ምንም ዓይነት ጥሪ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል።
እነዚህ የክልሉ ምክር ቤት ተመራጮች ይህን ቢሉም፤ የህወሓት ቃል አቃባይ የሆኑት አቶ ሚካኤለ አስገዶም ዛሬ ምሽት በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ የትግራይ ክልል የቀድሞው ምክር ቤት ስብሰባ በነገው ዕለት እንደሚካሄድ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። አቶ ሚካኤለ በዚሁ መልዕክታቸው፤ በክልሉ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የጸጥታ ችግር ወይም ፍንዳታ እንደደረሰ የሚያስወሩት “የትግራይ ጠላቶች ናቸው” ሲሉ ወንጅለዋል።
የመቐለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የዛሬው “የቦምብ ፍንዳታው ታቅዶ የተፈጸመ ነው” የሚል ጥርጣሬ ይኖራቸው እንደሁ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “እንደዚያ ብለን አላሰብንም። አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፣ ታስቦም ሊሆን ይችላል የሚለው በማጣራት ላይ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የፖሊስ አዛዡ ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ የተያዘ ተጠርጣሪ እንደሌለም ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































