በ2012 ዓ.ም የተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት፤ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ክልሉን እንዲመሩ ሾመ

ከስድስት ዓመት በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ የተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት፤ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 27፤ 2018 ባደረገው ስብስባ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾመ። በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ወደ ስራ እንዲመለስ የተደረገው ይኸው ምክር ቤት፤ ወ/ሮ ኪሮስ ሐጎስን አፈ ጉባኤ፣ ወ/ሮ ምህረት በርሀን ደግሞ ምክትል አፈጉባኤ አድርጎ መርጧል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅናው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የተሰረዘውን ህወሓት በሊቀመንበርነት የሚመሩት  ዶ/ር ደብረጽዮን፤ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት በአንድ ተቃውሞ እና በሶስት ድምጸ ተዐቅቦ፣ በአብላጫ ድምጽ እንደሆነ ፓርቲው ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ዶ/ር ደብረጽዮን በ2012 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ በተመረጠው ምክር ቤት በተመሳሳይ መልኩ ፕሬዝዳንት ተደርገው መሾማቸው ይታወሳል።  

ዶ/ር ደብረጽዮን ክልሉን እንዲመሩ በምክር ቤቱ የተሾሙት፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ወረደ የስልጣን ዘመን ለአንድ ዓመት ከተራዘመ ከሶስት ሳምንት በኋላ ነው። የጊዜያዊ አስተዳደሩን ለአንድ ዓመት በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ የቆዩት የሌተናል ጄነራል ታደሰን የስልጣን ዘመን ያራዘሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነበሩ። 

ከሌተናል ጄነራል ታደሰ በፊት በአቶ ጌታቸው ረዳ ሲመራ የቆየው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በጥቅምት 2015 ዓ.ም የተፈራረሙትን የግጭት ማቆም ስምምነት ተከትሎ ነው።  ህወሓት በ2012 ዓ.ም. የተመረጠውን ምክር ቤት ወደ ስራ በመመለስ የዛሬውን የፕሬዝዳንት ምርጫ ያካሄደው፤ “የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያ ስምምነትን አፍርሷል” የሚል ምክንያት በማቅረብ ነው። 

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወደ ስራ መመለስ በተመለከተ በዛሬው ስብሰባ ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ (ሞሽን)፤ በሁለት የምክር ቤት አባላት ድምጽ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን የህወሓት መግለጫ አመልክቷል። በዛሬው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ፤ “የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን” እና “ወቅታዊ ሁኔታዎችን” በተመለከተ የህወሓት ሊቀመንበር ሪፖርት ማቅረባቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል። 

ይህን ሪፖርት የክልሉ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ እንዳጸደቀው ፓርቲው አስታውቋል። ምክር ቤቱ ቀጥሎ የተመለከተውን የውሳኔ ሃሳብ ያጸደቀው ግን በአንድ ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዐቅቦ እንደሆነም ገልጿል። የውሳኔ ሃሳቡ ዶ/ር ደብረጽዮን እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ፤ በክልሉ ስራ አስፈጻሚ (ካቢኔ) ላይ “አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ” ስራቸውን እንዲቀጥሉ የሚጠይቅ ነበር።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ስብሰባውን ከማጠቃለሉ በፊት፤ በዛሬው ዕለት በአፈ ጉባኤነት ለተመረጡት ወ/ሮ ኪሮስ “ውክልና ሰጥቷል” ተብሏል። ወ/ሮ ኪሮስ የተሰጣቸው ውክልና፤ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ኮሚቴዎችን አዲስ ምደባ በመስጠት የማዋቀር ስራ እንዲያከናውኑ ነው። 

በመቐለ ከተማ የተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ፤ በከተማይቱ ላይ አንድ የጦር ጀት በረራ ሲያደርግ መታየቱ አነጋግሯል። አንድ ጀት በከተማይቱ ሰማይ ላይ ሲያንዣብብ የሚያሳዩ ቪዲዮችም በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በስፋት ተጋርተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሁለት የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች፤ ጀቱን ከርቀት መመልከታቸውን እና ድምጹንም መስማታቸውን አረጋግጠዋል። ከዚህ ክስተት አስቀድሞ በስብሰባው ዋዜማ፤ በመቐለ ከተማ የቦምብ ፍንዳታ መከሰቱ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሌላው መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

የትላንቱ ቦምብ ፍንዳታ የደረሰው በትግራይ ክልል ምክር ቤት እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት መካከል ባለ ቦታ ላይ እንደነበር የመቐለ ከተማ ፖሊስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። በፍንዳታው በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት አለመድረሱንም የከተማው ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)