“የታሰሩ ፋኖዎች ከእስር እንዲለቀቁ እየጠበቅን ነው”- መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ

መንግስት የታሰሩ ፋኖዎች ከእስር እንዲፈቱ “በገባው ስምምነት” መሰረት ትግበራውን እየጠበቁ መሆናቸውን የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) አመራር የነበሩት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ገለጹ። በአማራ ክልል የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ቆይተው በቅርቡ “ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል” መግባታቸውን የተናገሩት የአፋህድ አመራሮች፤ 17 አጀንዳዎችን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።

የአፋህድ አመራሮች አጀንዳዎቹን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያስረከቡት፤ ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ጋር ዛሬ ሐሙስ ጥር 28፤ 2018 በአዲስ አበባ ካካሄዱት ውይይት በኋላ ነው። ከአመራሮቹ መካከል ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ አፋህድን ወክለው ከአማራ ክልል መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ያስታወቁት መቶ አለቃ ማስረሻ ይገኙበታል። 

መቶ አለቃ ማስረሻ አፋህድን ወክለው የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ቢገለጽም፤ የድርጅቱ መሪ የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ ግን ግለሰቡ አስቀድመው ከድርጅቱ አመራርነታቸው መታገዳቸውን ማስታወቃቸው አይዘነጋም። አፋህድ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ መቶ አለቃ ማስረሻን እንዳልወከላቸው መግለጹም ይታወሳል።

በዛሬው የአጀንዳ ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት መቶ አለቃ ማስረሻ፤ ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል “በእስር ላይ ያሉ የፋኖ ታጣቂዎችን መፍታት” የሚለው አንዱ እንደነበር ተናግረዋል። በዚህ ስምምነት መሰረትም “የታሰሩ ፋኖዎች ከእስር እንዲለቀቁ እየጠበቅን ነው” ሲሉም አክለዋል።

የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ መቶ አለቃ ማስረሻ እና አጋሮቻቸው ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡ ያደረጓቸው ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ስለመመለሳቸው በምን እርግጠኛ ሆነው ወደ ስምምነት እንደመጡ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። “የአማራ ህዝብ እየደረሰበት ያለውን በደል” በመቃወም ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ትጥቅ ትግል መግባታቸውን የገለጹት መቶ አለቃ ማስረሻ፤ ያነሷቸውን ጥያቄዎች “በድርድር ለማስመለስ ሰላማዊ አማራጮችን ለመከተል ወስነናል” ብለዋል።

“ከጥያቄዎቻችን መካከል አንዱ የሆነው በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የሀገሪቱ ህገ መንግስት እንዲሻሻል የሚለው ዋነኛው ነው” ያሉት የአፋህድ አመራሩ፤ ነገር ግን ይሄ እና መሰል ጥያቄዎች “ጊዜ” እና “ሂደቶች” የሚጠይቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። “የትግል መንገድ ቀየርን እንጂ ትግሉ ይቀጥላል” ሲሉም ስለ በሰላማዊ አማራጭም ቢሆን ጥያቄያቸውን ከማቅረብ እንደማይቦዝኑ አብራርተዋል። 

የሰላማዊ የትግል አማራጭን በመከተል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ትጥቅ መፍታታቸውን የገለጹት የአፋህድ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሀባ በበኩላቸው፤ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች በሰላም ስምምነቱ መሰረት “በሰላማዊ መንገድ ይፈታሉ” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። በሰላም ስምምነቱ መሰረት ጥያቄዎቹ ካልተፈቱ ምን አካሄድ እንደሚከተሉ የተጠየቁት ኮሎኔል ፋንታሁን፤ አማራጩን አሁን ላይ ተሁኖ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል።

የአፋህድ ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ኢያሱ አባተ፤ ከመንግስት ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ “17 ሺህ ታጣቂዎች” በተሃድሶ ሂደት ውስጥ እያለፉ እንደሚገኙ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል። “አይደለም የእኛን አይነት ታጣቂ፤ ተራ ሽፍታ እንኳን ሰላምን ያውካል” ሲሉም ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣታቸው ለክልሉ ጸጥታ የሚኖረውን ፋይዳ አስገንዝበዋል። 

“ከባዱ ነገር ስርዓት መገንባት እንጂ ስርዓት ማፍረስ አይደለም። እኛ ወደ ትጥቅ ትግል የገባነው የተረጋጋ ስርዓት ለመገንባት እና ጥያቄዎቻችንን ለማስመለስ እንጂ አፍርሰን ወደኋላ ለመቅረት አይደለም” ሲሉም አቶ ኢያሱ አቋማቸውን አስረድተዋል። የአፋህድ አመራሮች ከመንግስት ጋር ካደረጉት ድርድር በተጨማሪ እንደ አማራ ህዝብ በመጪው ሀገራዊ ምክክር ላይ “በአጀንዳነት እንዲያዙ ያሏቸውን ጉዳዮች” ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቅረባቸውንም አክለዋል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የአፋህድ አመራሮች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ካቀረቧቸው 17 አጀንዳዎች መካከል “የአማራ ህዝብ የመጥፋት አደጋ ስጋቶች እንዲፈቱ” እና “የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች እንዲመለሱ” የሚሉት እንደሚገኙበት አቶ ኢያሱ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በአማራ ክልል ያለው “የመሰረተ ልማት ግንባታ” ጥያቄ እና ሌሎችም አጀንዳዎች ምክክር እንዲደረግባቸው መካተታቸውንም ገልጸዋል። 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኢትዮጵያዊያን በየጊዜው የሚገጥሟቸውን ሀገራዊ ችግሮች በምክክር እና ውይይት እንዲፈቱ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ “30 ዓመት” ያለፋቸው መሆኑን አስታውሰዋል። የትጥቅ ትግል አሸናፊ እና ተሸናፊን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው “ዛሬ ያሸነፈ ነገ ተሸናፊ በመሆኑ” ዘላቂ ሰላምን እንደማያመጣም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በኢትዮጵያ በምክክር እና በውይይት ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማምጣት ተቋም ከተመሰረተ ገና “አራት ዓመት” እንደሆነው የጠቆሙት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የሰራቸውን ስራዎች ለአፋህድ አመራሮች አብራርተዋል። በአማራ ክልል ባሉ 267 ወረዳዎች ከአምስት ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪዎች የተሳተፉባቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች መካሄዳቸውንም አመልክተዋል።  

በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች በሰላም እንዲጠናቀቁ፤ “በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት” ሚና እንደነበራቸው ዋና ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል። ለዚህ አስተዋጽኦቸውም በወቅቱ በትጥቅ ትግል ውስጥ ለነበሩት ለእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ምስጋና ቸረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)