ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተለያዩ ጊዜያት በሚያደርጓቸው ንግግሮች፤ ዓለም በኢትዮጵያ “እድገት እና ለውጥ ቢደመምም” በርካታ ኢትዮጵያውያን ግን የተሰራውን ስራ “በቅጡ ለመገንዘብ እና ለማድነቅ እንደሚያዳግታቸው” ሲናገሩ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ቅዳሜ ግንቦት 8፤ 2018 በተካሄደ አንድ ሁነት ላይ ባደረጉት ንግግርም ይህንኑ አቋማቸውን ደግመውታል።
አብይ ንግግሩን ያደረጉት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቃት መርሃ ግብር ላይ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ 14 ደቂቃ ገደማ በወሰደው ንግግራቸው፤ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ሰዎችን “ያስደሰተ” ያሉትን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት አንስተዋል።
ለእዚህ የእርሳቸው ገለጻ በማጣቀሻነት የቀረቡት፤ ባለፈው ሐሙስ በአዲስ አበባ ቆይታ አድርገው የነበሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ናቸው። ጉተሬዝ የመንግስታቱ ድርጅት የተመሰረተበት 80ኛ ዓመት የመታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉት” መካከል የሚመደብ መሆኑን ጠቅሰው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንቱ ንግግራቸው፤ ጉተሬዝ በንግግራቸው ያላካተቱን አሃዝ ጨምረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑን በአጽንኦት አስገንዝበዋል። “በቅርቡ ጉተሬዝ ሲናገር ሰምታችኋል። ኢትዮጵያ 10.2 ፐርሰንት የምታድግ ብቸኛ አገር ናት። በድፍን አፍሪካ 10.2 ፐርሰንት እድገት የሚያድግ አንድም ሃገር የለም” ብለዋል።
ይህ የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ አሃዝ፤ የፌደራል መንግስት ባለፈው ጥር ወር ባደረገው ክለሳ ላይ ይፋ ያደረገው ነው። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ በህዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ የፌደራል መንግስት በ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በ9 በመቶ ለማሳደግ “ይተጋል” ብለው ነበር።
ከእርሳቸው ንግግር አራት ወራት በኋላ ፓርላማ ፊት የቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዘንድሮው በጀት ዓመት ያስመዝግበዋል ተብሎ የሚጠበቀው እድገት ወደ 10.2 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን አስታውቀዋል። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ባለፈው ወር መጨረሻ ባወጣው ትንበያ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት 9.2 በመቶ እንደሆነ ገልጿል።

ተቋሙ ሀገሪቱ በሚቀጥለው ዓመት የምታስመዘግበው የኢኮኖሚ እድገት 7.9 በመቶ እንደሚሆንም ተንብይዋል። አይ ኤም ኤፍ እና የፌደራል መንግስት በሚያወጧቸው ትንበያዎች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከዚህ ቀደም በበጎ ጎን ሲጠቅሱት ተደምጠዋል።
አብይ በትላንቱ ንግግራቸው ላይ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች፤ በኢትዮጵያ የሚታየው እድገት እና ለውጥ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ዜጎችን “የሚያስደምም” እንደሆነ ገልጸዋል። “ሰዎች ከአውሮፓ እየመጡ፣ ከአሜሪካ እየመጡ፣ በእናንተ ሀገር እድገት እየተደነቁ፣ እየተደመሙ፤ እናንተ ‘አላየንም፣ አልሰማንም’ አትበሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በኢትዮጵያ ባለው ስራ እና ለውጥ “ዓለም እየቀና፣ እየተደነቀብን ባለ በዚህ ጊዜ ውስጥ፤ እኛ አይናችን ከታወረ ለማደግ እንቸገራለን” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሚያዝያ ወር ከብሔራዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ተመሳሳይ ይዘት ያለው መልዕክት አስተላልፈው ነበር። አብይ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው “ብዙ ሰዎች አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በደንብ የሚገባቸው አይመስለኝም። ዝም ብሎ ሲናገሩ ስሰማ፤ እየተጓዝን ያለንበት ሩጫ ፍጥነት ውጤት የሚገባቸው አይመስለኝም” ሲሉ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































