በትግራይ ክልል “በአጭር ጊዜ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲኖር” ለማድረግ ያለመ ምክር ቤት ተቋቋመ

በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ በይፋ የተመሰረተው የትግራይ “የሰላም እና የለውጥ ምክር ቤት” ዋና ዓላማ፤ በክልሉ “በአጭር ጊዜ ውስጥ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲኖር ማድረግ” መሆኑን ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። ምክር ቤቱ እስከ 40 የሚደርሱ አባላት የሚይዝ ሲሆን አስተባባሪ ኮሚቴም ተዋቅሮለታል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የሲቪክ ማህበራት እና የሚዲያ አካላትን የያዘው ምክር ቤት፤ የምስረታ መርሃ ግብሩን ያከናወነው በአዲስ አበባ በሚገኘው ካሌብ ሆቴል ነው። በትላንቱ የምስረታ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ ህገ-ደንብ እና ማኒፌስቶ የጸደቀ ሲሆን የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላትም ተመርጠዋል። 

የስምረት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሀፍቱ ኪሮስ፤ በምክር ቤቱ ውስጥ እርሳቸው አመራር የሆኑበትን ጨምሮ ወለዶ ትግራይ፣ ትንሣኤ ሰባ እንደርታ፣ ውድብ ነጻነት ትግራይ (ውነት)፣ ዓባይ ትግራይ እንዲሁም አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (አረና) ፓርቲዎች እንደሚገኙበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በትላንቱ የምስረታ ስብሰባ ላይ የትግራይ ሰላም ኃይል አባላት መካከል የተገኙ ግለሰቦች ቢኖሩም  ስብስቡ የምክር ቤቱ አባል እንዳልሆነ አቶ ሀፍቱ ገልጸዋል።

እዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ሲል “በተናጠል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሲያደርጉ” መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ ሀፍቱ፤ በአንድ ምክር ቤት ስር ለመሰባሰብ የወሰኑት “የጋራ አቅም ለመፍጠር” እና “እንደ አንድ አደረጃጀት በጋራ ለመታገል” እንደሆነ አስረድተዋል። ፓርቲዎቹ “በተናጠል ያደርጓቸው የነበሩትን የሚዲያ የፕሮፓጋንዳ እና የአደረጃጀት አቅሞች በማስተባበር”፤ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልልን “ጠቅልሎ የያዘ ህግ-አልባ ኃይልን” ላይ ለመታገል ምክር ቤቱን ማቋቋማቸውንም አመልክተዋል። 

“[ምክር ቤቱ] ትግራይ ውስጥ ያለውን አምባገነን፣ ህግ የማያውቅ፣ ህግ አልቦ ኃይልን ማስወገድ፣ የሰላም እና የማረጋጋት ስራ የሚሰራ ብሎም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትግራይ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲኖራት የማድረግ ስራን ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው” ሲሉ አዲሱ አደረጃጀት የተመሰረተበትን ዋና ዓላማ አቶ ሀፍቱ አብራርተዋል። የጋራ ጥምረቱ “በምርጫ ቦርድ የታወቀ ፓርቲ እና ኃይል በሌለበት ሁኔታ ‘ትግራይ የእኔ ንብረት ነች፤ የእኔ እቃ ነች’ በሚል የሚንቀሳቀሰውን ህገወጥ ቡድን ለመታገል የተመሰረተ” መሆኑንም አክለዋል። 

የስምረት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት “አሁን ላይ ትግራይ ውስጥ እየመራ ያለ ፓርቲ የለም። የሆነ ህገወጥ ቡድን ነው ያለው” ሲሉም፤ ከሳምንት በይፋ የክልሉን ስልጣን መቆጣጠሩን ያወጀውን የህወሓት ኃይል በስም ሳይጠቅሱ አጣጥለዋል። ህወሓት የትግራይ ክልልን የመምራት ኃላፊነት መረከቡን ያስታወቀው፤ ሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በክልሉ ምክር ቤት መሾማቸውን ተከትሎ ነው።

ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደ አወዛጋቢ ምርጫ የተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ሹመቱን የሰጠው፤ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ምክር ቤቱ ወደ ስራ እንዲመለስ ባለፈው ወር ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ባካሄደው ጉባኤ ነው። በዚህ መልኩ በምክር ቤቱ የተሾሙት ዶ/ር ደብረጽዮን የካቢኔ ስብሰባዎችን በተከታታይ በማድረግ እና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ፤ ክልሉ በእርሳቸው ቁጥጥር ስር መሆኑን የሚያሳዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

የስምረት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል “ጦርነት ከሚያደርሰው በላይ ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የትግራይ ክልል “የፌዴሬሽኑ አባል ነው ለማለት እጅግ በጣም በሚያስቸግር ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ” የገለጹት አቶ ሀፍቱ፤ የክልሉ ህዝብም እስካሁን ሲተዳደር የቆየው በፌደራል መንግስት በተሰጠው ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሆነ አመልክተዋል።

“የትግራይ ህዝብ በፕሪቶሪያው ስምምነት አግኝቶት የነበረውን አንጻራዊ ሰላም አጥቷል” የሚሉት አቶ ሀፍቱ፤ ይህ ችግር የሚፈታው “በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ አይደለም” በሚል እሳቤ “የትግራይን አጀንዳ ይዘን እንቀሳቀሳለን” የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማቋቋማቸውን አብራርተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በምክር ቤቱ ጥላ ስር አንድ የጋራ ማኒፌስቶ አዘጋጅተው በትላንቱ ስብሰባ ላይ ማጽደቃቸውንም አስረድተዋል።  

በምክር ቤቱ ማኒፌስቶ ውስጥ ከተቀመጡት ቅድመ-ሁኔታዎች ውስጥ፤ በአባልነት የሚመዘገብ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ “በምርጫ ቦርድ የታወቀ፣ ህግና ሕገ-መንግሥትን የሚያከብር እንዲሁም በትግራይ ሕዝብ ጥቅም ላይ የማይደራደር መሆን አለበት” የሚል እንደሚገኝበት አቶ ሀፍቱ ገልጸዋል። የጸደቀው ማኒፌስቶ እርሳቸው “ህገወጥ” ብለው የሚጠሩን ኃይል “ማስወገድ ብቻ ሳይሆን”፤ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ የሰላም እና ማረጋጋት ስራዎችን ማከናወን እንደሚያካትትም ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል በአጭር ጊዜ ውስጥ “በህዝብ ይሁንታ የተመረጠ መንግስት እንዲመሰረት” “እኩል የፖለቲካ ምህዳር” የመፍጠር ዓላማ እንዳለውም አስገንዝበዋል። የምክር ቤቱ መመስረት ፓርቲዎች አንዳቸው የሌላቸውን ፕሮግራም ለማወቅ እድል ይሰጣል ያሉት አቶ ሀፍቱ፤ “በየትኛው ጉዳይ ላይ ‘አብሮ መስራት ይቻላል ወይም አይቻልም’ የሚለውን ለይቶ እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ እና በመካከላቸው ያለው ቅንጅት እንዲጠነክር” ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

የትግራይ “የሰላም እና የለውጥ ምክር ቤት” አባላት ብዛት በአሁኑ ወቅት 40 መሆኑን የገለጹት የስምረት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ቁጥሩ ወደ 45 ከፍ ሊል እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። እነዚህ አባላት በምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ስር እንደሚሳተፉም አቶ ሀፍቱ ተናግረዋል። 

“ሶስት ወር የሚያቆይ አይደለም ያለን ችግር። አሁን በጣም አንገብጋቢ ችግር ነው ያለው። ትግራይ ከዚያም በፊት እየተሰበሰበ፣ እየመከረ፣ የትግል አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ እና ኃይል እያሰባሰበ፣ ትግሉን ፈጠን ባለ ጊዜ ወደ መጨረሻው የሚያደርስበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል መግባባት ላይ ደርሰናል”

በጋራ ጥምረቱ አደረጃጀት መሰረት፤ ምክር ቤቱ የፖለቲካ፣ የፋይናንስ፣ የኮሚኒኬሽን፣ የአደረጃጀት እና የስትራቴጂ ጉዳዮችን የሚመለከቱ አምስት የሚሆኑ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ይኖሩታል። እነዚህ አስተባባሪ ኮሚቴዎች በየሁለት ሳምንቱ፣ ዋናው ምክር ቤቱ ደግሞ በየሶስት ወሩ እንዲሰበሰብ በምክረ ሃሳብ ደረጃ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፤ በትላንቱ ስብስባ ላይ ግን ይህ አሰራር ማስተካከያ እንዲደረግበት ከመግባባት ላይ መደረሱን አቶ ሀፍቱ ገልጸዋል።  

“ሶስት ወር የሚያቆይ አይደለም ያለን ችግር። አሁን በጣም አንገብጋቢ ችግር ነው ያለው። ትግራይ ከዚያም በፊት እየተሰበሰበ፣ እየመከረ፣ የትግል አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ እና ኃይል እያሰባሰበ፣ ትግሉን ፈጠን ባለ ጊዜ ወደ መጨረሻው የሚያደርስበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል መግባባት ላይ ደርሰናል” ሲሉ የስምረት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)