ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ለ64 የፓርላማ መቀመጫዎች ብቻውን ለምርጫ መቅረቡ ታወቀ

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ግንቦት መጨረሻ በሚደረገው ምርጫ፣ በአምስት ክልሎች በሚገኙ 64 የምርጫ ክልሎች ብቻውን ለፓርላማ እንደሚወዳደር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላትንናው ዕለት ይፋ ያደረገው ሰነድ አመለከተ። ከእነዚህ የምርጫ ክልሎች ውስጥ አርባ ስድስቱ በኦሮሚያ፣ አስራ አንዱ ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው። 

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የምርጫ ቦርድ ሰነድ፤ በሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር የዕጩነት ምዝገባ የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ዕጩዎች ዝርዝርን የያዘ ነው። ለፓርላማ እና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ዝርዝር በያዘው በዚህ ሰነድ ውስጥ የሐረሪ እና የትግራይ ክልሎች መረጃ አልተካተተም።

የዕጩዎች መረጃ ይፋ ከተደረገባቸው 10 ክልሎች መካከል በአምስቱ ብቻውን በተወዳዳሪነት የቀረበ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ የለም። በስራቸው ባሉ ሁሉም ምርጫ ክልሎች በእያንዳንዳቸው ከአንድ በላይ ተወዳዳሪ የቀረበባቸው ክልሎች አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ናቸው። 

አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችም በተመሳሳይ መልኩ፤ በሁሉም የምርጫ ክልሎቻቸው ከአንድ በላይ ዕጩዎች ለውድድር ቀርበዋል። አዲስ አበባ ካሏት 23 የምርጫ ክልሎች በሦስቱ ገዢው ፓርቲ ለፓርላማ ዕጩዎችን ባያቀርብም፣ ዘጠኝ ፓርቲዎች ለእነዚህ መቀመጫዎች ተወዳዳሪዎችን ማስመዝገባቸውን የምርጫ ቦርድ ሰነድ ያመለክታል። 

ዝርዝር ዘገባውን ከ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethioelections.com/2026/05/17591/