ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ ምርት ካለፈው ዓመት በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ  

በዘንድሮው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ማዕከላዊው ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን፤ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ብልጫ ማሳየቱ ተገለጸ። ብሔራዊ ባንክ ለወርቅ አቅራቢዎች የሚከፍለውን ማበረታቻ ማሳደጉ፤ ለክልሉ የወርቅ አቅርቦት መጨመር በዋና ምክንያትነት ተጠቅሷል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ከልዩ አነስተኛ እና ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለመሰብሰብ ያቀደው 3,525 ኪሎ ግራም ወርቅ ነበር። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ከትላንት በስቲያ እሁድ ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት፤ በመንፈቅ ዓመት ውስጥ ለብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን 4,158.6 ኪሎ ግራም እንደሆነ አስታውቀዋል። 

ይህ አኃዝ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ ብሔራዊ ባንክ ከገባው 1,697.68 ኪሎ ግራም ወርቅ ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቱጃኒ አዳም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ብሔራዊ ባንክ ለወርቅ አቅራቢዎች የሚከፍለውን ማበረታቻ ማሳደጉ ተከትሎ፤ አምራቾች ምርታቸውን ወደ ህጋዊ መስመር በማስገባታቸው የክልሉ የወርቅ አቅርቦት መጨመሩን ኃላፊው አስረድተዋል። 

ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ባሻሻለው የወርቅ ግዢ መመሪያ፤ ለባንኩ የሚቀርበው የወርቅ መጠን ከአምስት ኪሎ ግራም በላይ ከሆነ ከዓለም አቀፍ ዋጋ ላይ 15 በመቶ ጭማሪ በማድረግ እንደሚገዛ አስታውቆ ነበር። በተመሳሳይ መልኩ ከ250 ግራም ጀምሮ እስከ አምስት ኪሎ ግራም ወርቅ ለሚያቀርቡ አቅራቢዎች፤ ከዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ አምስት በመቶ ጭማሪ በማድረግ ክፍያ እንደሚፈጽም ባንኩ በወቅቱ ገልጿል።

ይህ ማበረታቻ ካመጣው ለውጥ ሌላ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለበርካታ “ልዩ አነስተኛ” አምራቾች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የስራ ፈቃድ መስጠቱ፤ ለክልሉ የወርቅ አቅርቦት ማደግ በተጨማሪ ምክንያትነት ተጠቅሷል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ወርቅ አምራቾች፤ “ልዩ አነስተኛ” እና “ባህላዊ” በሚሉ ደረጃዎች የተከፋፈሉ ናቸው።

በ“ልዩ አነስተኛ” ደረጃ የሚገኙ ወርቅ አምራቾች ፍቃድ የሚወስዱት ከክልሉ ማዕድን ቢሮ ሲሆን ባህላዊ አምራቾች ግን በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው የስራ ፈቃድ የሚያገኙት ከወረዳ ጽህፈት ቤቶች ነው። በክልሉ በአሁኑ ወቅት 50 የባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበራት እንዳሉ ከክልሉ ማዕድን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከአንድ ሄክታር በታች በሆነ ይዞታ ላይ የሚንቀሳቀሱት ባህላዊ አምራቾች፤ ምርታቸው “ከእጅ ወደ አፍ” መሆኑን አቶ ቱጃኒ ይናገራሉ። “በገበቴ ወንዝ ላይ ነው የሚሰሩት። ምርታቸው በባህላዊ ስለሆነ ብዙ ግራም ወርቅ አያገኙም። አንድ፣ ሁለት ግራም [ቢያገኙ ነው]” ሲሉ የቢሮ ኃላፊው ስለ እነዚህ አምራቾች ሁኔታ ያስረዳሉ።

ባህላዊ አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ መሸጥ ስለማይችሉ፤ የወርቅ ምርቱ በጥቁር ገበያ እንዳይሸጥ ቁጥጥር እንደሚደረግ አቶ ቱጃኒ ይገልጻሉ። ባህላዊ አምራቾቹ ፈቃድ ላላቸው የወርቅ አቅራቢዎች እንዲያስረክቡ እንደሚደረግም ያክላሉ።  

እስከ አምስት ሄክታር ባለ ይዞታ  ወርቅ የሚመርቱት “ልዩ አነስተኛ” አምራቾች በአንጻሩ ምርታቸውን በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ የማቅረብ ፍቃድ ያላቸው ናቸው። በዚህ ደረጃ ወርቅ ለሚያመርቱ አምራቾች የክልሉ ማዕድን ቢሮ ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት የሚሰጠው ፍቃድ ከ200 የማይበልጥ እንደነበር የሚገልጹት ኃላፊው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 530 ለሚሆኑ አምራቾች ፍቃድ መሰጠቱን አስረድተዋል።

ለ“ልዩ አነስተኛ” አምራቾች  የሚሰጠው ፈቃድ መጨመሩ፤ በክልሉ “በህገ ወጥ መንገድ” ይከናወን በነበረው የወርቅ ማውጣት እና መሸጥ ተግባር ላይ የመቆጣጠር ስራ ለመስራት እንዳስቻለ አቶ ቱጃኒ ጨምረው ገልጸዋል። በዘንድሮው በጀት ዓመት በተደረገው የክትትል እና የቁጥጥር ስራ፤ “በህገ ወጥ መንገድ” እና “በማን አለብኝነት” በወርቅ ማዕድን ማውጣት ላይ የተሰማሩ አካላቶች እርምጃ መወሰዱን የቢሮ ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

 “ቦታው ድረስ በመገኘት [እንደተመለከትነው] በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ አሉ። ብዙ ማሽኖች እና ሌሎች ወርቅ መስሪያ ቁሳቁሶች ላይ እርምጃ ወስደናል” የሚሉት አቶ ቱጃኒ፤ ይህ አካሄድ በርካታ አምራቾች ወደ ህጋዊ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ “አስቻይ ሁኔታ” እንደፈጠረ አብራርተዋል። አምራቾቹ ወደ ህጋዊ ስርዓት መምጣታቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለፌደራል መንግስት የሚያስገባውን የወርቅ መጠን እንዲጨምር ለማድረጉ አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነም አመልክተዋል። 

የፌደራል መንግስት በ2018 በጀት ዓመት ሶስት ወራት በኢትዮጵያ ይመረታል በሚል በዕቅድ አስቀምጦት የነበረው የወርቅ መጠን 8.37 ቶን ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከእቅድ በላይ የተመረተው 11.47 ቶን ወርቅ፤ ለሀገሪቱ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳስገኘ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ባለፈው ጥቅምት ወር አስታውቀው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)