ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “የመንግስት ስልጣንን ይዣለሁ ብሎ ስልጣን በሌላ መንገድ ለመቀጠል ፈጽሞ አያስብም” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ምርጫ የከተማይቱ ነዋሪ ለፓርቲው ድምጽ እንዲሰጥ ለማሳመን “በብዙ መንገድ እየሰራ” መሆኑንም ገልጸዋል።
ከንቲባዋ ይህን የገለጹት ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ በአዲስ አበባው መስቀል አደባባይ በተከናወነው የብልጽግና ፓርቲ የምረጡኝ ቅስቅሳ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ባሰሙት ንግግር ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ የዘንድሮው ምርጫ የምረጡኝ ዘመቻ ነገ ረቡዕ ግንቦት 19፤ 2018 ይጠናቀቃል።
ከንጋት ጀምሮ በተከናወነው በዛሬው መርሃ ግብር፤ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች፣ የገዢው ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ተገኝተዋል። ከንቲባ አዳነች በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በመስቀል አደባባይ የተገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች “የብልጽግና ፓርቲን ከመደገፍ ባለፈ አንድ ትልቅ መልዕክት ለዓለም አስተላልፏችኋል” ብለዋል።

“ኢትዮጵያውያን በምርጫ ብቻ እንደሚያምኑ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት እንደሚችሉ፤ መንግስትን በምርጫ፣ በህዝብ ይሁንታ ማጽናት የሚችሉ ብርቱ ህዝቦች መሆናቸውን ለዓለም ነግራችኋል፣ አስመስክራችኋል” ሲሉ አዳነች ለነዋሪዎቹ ምስጋና አቅርበዋል። የነዋሪዎቹ መልዕክት ከንቲባዋ “ባንዳ” ላሏቸው ኃይሎች ጭምር የተላለፈ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
“ከምርጫ ውጪ ስልጣንን ለማግኘት ሲሉ፣ በባንዳነት ለተለያዩ የኢትዮጵያ ጠላቶች ለሚያገለግሉትም እንዲሁም ስልጣንን በጉልበት ለመያዝ ሀገራችንን የተለያየ ቦታ ላይ ለሚረብሹትም፤ ጽኑ እምነታችሁን ‘ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ብቻ’ ብላችሁ ዛሬ እነሆ ምላሽ ሰጥታችኋል” ሲሉም ከንቲባዋ ተናግረዋል። የሰባተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ “ስልጣን በምርጫ እንጂ በጉልበት ወይም ደግሞ እንደ ቅርጫ የሚከፋፈል አለመሆኑን የምናስመሰክርበት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ጥር ወር በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ መንግስታቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን የተቃዋሚ ፓርቲ ድምጾች “በአምስት እና በአስር እጥፍ” ለመጨመር “ይሁነኝ ብሎ” እንደሚሰራ ገልጸው ነበር። ይህንን ተከትሎም ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባ በፓርላማ ካላት መቀመጫዎች ውስጥ በሶስቱ፣ ከከተማይቱ ምክር ቤት ወንበሮች ደግሞ በ24ቱ ተወዳዳሪዎቹን ሳያቀርብ ቀርቷል።

ይህ የገዢው ፓርቲ እርምጃ “የምክር ቤት መቀመጫዎችን በማከፋፈል የሚፈልጋቸውን ፓርቲዎች ዕጩዎች እና የግለሰብ ተወዳዳሪዎችን ለማስመረጥ ያደረገው ነው” የሚል ትችትን አስከትሎበታል። የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስት አካላት የምርጫ ካርድን “የማህበራዊ አገልግሎት እና ደመወዝ ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ” እና “ቤት ለቤት በመዘዋወር ‘ካርድ ውሰዱ’ በሚል ህግን የሚጥስ ተግባር ፈጽመዋል” የሚሉ ውንጀላዎች ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
ከንቲባ አዳነች በዛሬው ንግግራቸው ለእነዚህ ውንጀላዎች ምላሽ የሚመስል ገለጻ ተጠቅመዋል። “ብልጽግና የመንግስት ስልጣንን ይዣለሁ ብሎ ስልጣን በሌላ መንገድ ለመቀጠል ፈጽሞ አያስብም” ያሉት አዳነች፤ “ለዚህ ነው ‘ዳግም ምረጡን’ እያልን፣ ሌት እና ቀን የምንጎተጉታችሁ” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“እንድትመርጡን እናንተን ለማሳመን በብዙ መንገድ እየሰራን ያለነው፤ ከእናንተ ድምጽ ውጪ ዳግም ወደ ስልጣን መመለስ የምንችልበት ምንም መንገድ እንደሌለ ስለምናምን ነው” ሲሉም ክንቲባዋ አክለዋል። ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እና ለከተማይቱ የፓርላማ መቀመጫዎች በአጠቃላይ 154 ዕጩዎችን ለውድድር አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































