ቱርክ በአፍሪካ ቀንድ “አዲስ ግጭቶች” “በፍጹም” ማየት እንደማትፈልግ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

ቱርክ በአፍሪካ ቀንድ “አዲስ ግጭቶች” “በፍጹም” ማየት እንደማትፈልግ እና በቀጠናው “ስቃይ ውስጥ በሚገኙ” ሰዎች ላይ “አዲስ ህመም” መጨመር እንደማይገባ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች “የመፋለሚያ ሜዳ” ሊሆን እንደማይገባም አሳስበዋል። 

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ማሳሰቢያውን የሰጡት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ኤርዶኻን ከ11 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የገቡት፤ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 10፤ 2018 ከሰዓት በኋላ ነበር።

በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጉብኝት አቀባበል እና ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በብሔራዊው ቴሌቪዥን በቀጥታ ተላልፏል። ኤርዶኻን ሰባት ደቂቃ በፈጀው የተጻፈ ንግግራቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የአፍሪካ ቀንድ ሰሞነኛ የፖለቲካ ሁኔታ ይገኝበታል። 

ፎቶ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተወሰደ

“የዓለም ሁሉ አይን በአፍሪካ ቀንድ ላይ ባረፈበት በዚህ ጊዜ፤ የኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ የሀገረ መንግስት መዋቅር እና ተምሳሌታዊ አስተዳደር የበለጠ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል” ያሉት ፕሬዝዳንት ኤርዶኻን፤ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ቱርክ ያላትን አቋም አያይዘው ግልጽ አድርገዋል። “ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጠና ያሉ ሀገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት አስፈላጊነት ላይ፤ ያለንን አቋም በተለይ አጽንኦት መስጠት እፈልጋለሁ” ብለዋል የቱርኩ ፕሬዝዳንት።

ኤርዶኻን ይህን ያሉት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል “ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል” ተብሎ በተሰጋበት በዚህ ወቅት ነው። ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን በተደጋጋሚ ማንጸባረቋን ተከትሎ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለፉት ወራት ፖለቲካዊ ውጥረት ተፈጥሮ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም፤ ይህንኑ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል። አብይ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው “ዘለግ ያለ” ውይይት ላይም፤ ለኢትዮጵያ የባህር ተደራሽነት ፍላጎት ኤርዶኻን “የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ” መጠየቃቸውን አስታውቀዋል።

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

“ከ130 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ሀገር sea access ተከልክላ፤ በዓለም ላይ ካለው ልምምድ እና ትሬንድ ውጪ በጠላቶቻችን ደባ፣ ለረዥም ጊዜ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና እንድትቆይ መደረጉ ትክክል አለመሆኑን እና እንደ ቱርኪዬ ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጆች በዲፕሎማቲክ መስኩ ጫና በመፍጠር፤ በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያ የsea access ማግኘት የምትችልበትን ሁኔታ እንዲያግዙ በስፋት ተወያይተናል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ እድገት “ሎጂስቲክስ” አንዱ ትልቁ “ማነቆ” እንደሆነ የጠቀሱት አብይ፤ ሀገሪቱ ለባህር ተደራሽ መሆኗ “ቁልፉን ነገር የሚይዝ” እንደሆነ አስታውቀዋል። በዚህ ጉዳይ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጋር የነበራቸውን ውይይት “ጠንከር ያለ” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኤርዶኻን በዚህ ረገድ ለሚጫወቱት ሚና ምስጋናቸው አቅርበዋል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ለጋዜጠኞች በንባብ ባሰሙት ንግግራቸው ላይ የኢትዮጵያን የባህር በር ተደራሽነት ጥያቄን በቀጥታ አላነሱም። ሆኖም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በተመሳሳይ ጉዳይ የገቡበትን ወዝግብ፤ በአንካራ ከተማ ባደረጉት ስምምነት ለነበራቸው ተሳትፎ አመስግነዋል። 

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ልዩነቶቻቸውን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ ለመተው” እና “ትብብር ለማበጀት” በአንካራ ስምምነት የተፈራረሙት በታህሳስ 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር። ሁለቱ ሀገራት በቱርክ አመቻችነት በተፈራረሙት በዚሁ ስምምነታቸው፤ “አንዳቸው ለሌላው ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት ያላቸውን ክብር እና ቁርጠኝነት” መግለጻቸው ይታወሳል። 

ቱርክ ሁለቱን የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት ያሸማገለችው፤ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር “የአጋርነት እና የትብብር ስምምነት” ከተፈራረመች በኋላ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውጥረት ለመፍታት ነበር። ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ በታህሳስ 2016 ዓ.ም  የተፈራረሙት ስምምነት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ መንገዱን የጠረገ ነበር።

ስምምነቱ በአንጻሩ ለሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ እውቅና እንደሚያስገኝላት በወቅቱ ተገልጿል። ይህን ስምምነት “ሶማሌላንድ የግዛቴ አካል ነች” የምትለው ሶማሊያ አጥብቃ ማውገዟን ተከትሎ፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያው ግንኙነት እስከ አንካራው ስምምነት ድረስ ሻክሮ ቆይቷል።

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ከአንካራው ስምምነት በኋላ የሶማሌላንድ እውቅና የማግኘት ጉዳይ በኢትዮጵያ በኩል ያበቃለት ቢመስልም፤ እስራኤል ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ለራስ ገዝ አስተዳደሯ የሀገርነት እውቅና በመስጠት የመጀመሪያ ሆናለች። ይህንን የእስራኤል እርምጃ አጥብቀው ከተቃወሙት ውስጥ ቱርክ አንዷ ነች። 

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም የቱርኩ ፕሬዝዳንት እስራኤል የሰጠችው እውቅና “ለሶማሌላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ፋይዳ ቢስ ነው” ሲሉ የሀገራቸውን አቋም በድጋሚ አስተጋብተዋል። የእስራኤልን ጉዳይ ከማንሳታቸው አስቀድሞ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የውጭ “የመፋለሚያ ሜዳ” ሊሆን እንደማይገባም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ችግር መፍትሔ ማግኘት ያለበት በቀጠናው ሀገራት “በራሳቸው” መሆን እንዳለበትም ኤርዶኻን አጽንኦት ሰጥተዋል። የቱርኩ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉበኝት፤ ለቀጠናው “ሰላም” እና “መረጋጋት” አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋቸው ገልጸዋል። “ከዚህ ጉብኝት አዎንታዊ ውጤት እንደምናገኝ እርግጠኛ ነኝ” ሲሉም ተደምጠዋል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ከተመለሰ፤ ቀጠናው ባሉት ኢኮኖሚያዊ እድሎች “ትኩረት እንደሚስብ” እና በዚህ ረገድም “ምንም አይነት እንቅፋት” እንደማይታያቸው ኤርዶኻን በንግግራቸው አስገንዝበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጋር መግባባት ላይ ከደረሱባቸው “ወሳኝ ጉዳዮች” መካከል፤ ኢኮኖሚዊ ጉዳይ አንዱ መሆኑን ከኤርዶኻን ቀድመው በአማርኛ ቋንቋ በሰጡት መግለጫ ላይ አመልክተው ነበር።

“በኢትዮጵያ እና በቱርክ መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጣችን ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር መሙላት እንዲችል እና ከዚያም በላይ ማደግ እንዲችል፤ በሁለቱም መንግስታት ታቅዶ እንዲሰራበት እንዲሁም የቢዝነስ ሴክተሮች diversify እንዲደረጉ እና በሁለታችን መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እንዲያድግ ከስምምነት ተደርሷል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል።

የቱርክ “ሁነኛ ኩባንያዎች” ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት “ኢንቬስት” እንዲያደርጉ ከኤርዶኻን ጋር መነጋገራቸውንም አብይ አክለዋል። ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የቱርክ ኩባንያዎች እና ተጨማሪ ኢንቬስተሮች፤ “ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ገበያ ኤክስፖርት ማድረግ እንዲችሉ” በትብብር ለመስራት መስማማታቸውንም ገልጸዋል።

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

በኢትዮጵያ እና በቱርክ መካከል ያለው የንግድ መጠን ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በአምስት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን “ዴይሌ ሳባህ” የተሰኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል። ለቱርክ መንግስት ቅርበት ያለው ይኸው ጋዜጣ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግል መጠን በአሁኑ ወቅት 253 ሚሊዮን ዶላር መድረሱንም ዛሬ ባወጣው ዘገባ ላይ ጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]