የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን በስምንት ወር አራዘመ። ፓርላማው የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለሁለተኛ ጊዜ ያራዘመው፤ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 11፤ 2018 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ነው።
በታህሳስ 2014 ዓ.ም በወጣ አዋጅ የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ መጀመሪያ የተሰጠው የሶስት ዓመት የስራ ዘመን ነበር። ኮሚሽኑ በተሰጠው ጊዜ ስራውን ማገባደድ ባለመቻሉ፤ በየካቲት 2017 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ በተካሄደ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ አንድ ዓመት እንደተጨመረለት ይታወሳል።
የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለዕረፍት ከተበተኑበት ተጠርተው ባካሄዱት በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የአራት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦላቸው ውይይት አድርገውበታል። ውይይቱን ተከትሎ የምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ያደመጡት የፓርላማ አባላቱ፤ የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለሁለተኛ ዙር እንዲራዘም በሙሉ ድምጽ ወስነዋል።
ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች “ወሳኝ ምክንያቶችን የመለየት” እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት “ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት” ተልዕኮ ተሰጥቶት የተቋቋመው ኮሚሽኑ፤ ከዕቅዱ 93 በመቶ ያህሉን ማሳካቱን ከአንድ ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር። ኮሚሽኑ ከቀሩት ዋነኛ ስራዎች መካከል፤ ከትግራይ ክልል ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎች ማሰባሰብ ይገኝበታል።
ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያካሄደው የምክክር ጉባኤም እንደዚሁ የሚጠበቅ ነው። ከአስር ቀን በፊት የፓርላማው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው ስብሰባ ላይ የተገኙት፤ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ “ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ስኬታማ እንዲሆን [ተጨማሪ] ጊዜ ያስፈልጋል” ማለታቸው የሚታወስ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]






























