የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የትግራይ ክልል የምክክር ሂደትን በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚኖሩ እና ከክልሉ ለሚመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ከፍተኛ ጥሪ” በማድረግ የምክረ-ሐሳብ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ለማከናወን ማቀዱን አስታወቀ። መርሃ ግብሩን በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ለማካሄድ መታቀዱን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በታህሳስ 2014 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመው፤ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች “ወሳኝ ምክንያቶችን የመለየት” እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት “ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት” ዓላማ ይዞ ነው። ኮሚሽኑ እስካሁን ድረስ ከ11 ክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ ከፌደራል እና ከዳያስፖራ የተሰበሰቡ የምክክር አጀንዳዎችን ማሰባሰብ ችሏል።
ትላንት ረቡዕ የካቲት 11፤ 2018 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የኮሚሽኑን የአራት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ኮሚሽኑ መድረስ ከነበረበት 1,332 ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች 93 በመቶ በሚሆኑት የህብረተሰብ ተወካዮች በማስመረጥ እና አጀንዳዎችዎችን በማሰባሰብ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ዝግጁ ማድረጉን አስታውቀዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በትግራይ ክልል ተሳታፊ የመለየት ሂደትን ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ይህ አለመከናወኑን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን በዚሁ ሪፖርታቸው፤ በትግራይ ክልል ባለው “ነባራዊ ሁኔታ” የኮሚሽኑን የአሳታፊነት እና አካታችነት መርህን ተደራሽ ለማድረግ መቸገራቸውን ተናግረዋል። በትግራይ ክልል የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ለማካሄድ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቐለ ከተማ ውይይቶችን ማድረጉንም አስረድተዋል።
ሆኖም በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል በሚቀመጡ “ተከታታይ ቅድመ ሁኔታዎች” የተነሳ “ምቹ ሁኔታ” መፍጠር እንዳልተቻለ ዋና ኮሚሽነሩ ለፓርላማ አባላት ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በአሁኑ ወቅት እየመሩ ከሚገኙት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ጋር ባደረጉት ንግግርም፤ ምክክሩን ለማድረግ ህብረተሰቡን “በቀላሉ ለማግኘት” የሚቻልባቸው መቐለ፣ አዲግራት፣ ማይጨው፣ ሽሬ እና አክሱም ከተሞች እንደሆኑ ተገልጾላቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።
በዚህ መሰረት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ “ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ” የነበረ ቢሆንም፣ በህጻጽ ተፈናቃዮች ካምፕ በተፈጠረ ወቅታዊ ችግር ምክንያት ሂደቱን ለማከናወን የሚያስችል ፈቃድ ሳይገኝ እንደቀረ አስታውቀዋል። “የህጻጽ ጉዳይ ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ ከእርሳቸው ጀምሩ የሚለውን ፈቃድ ስላላገኘን [ሳይካሄድ ቀርቷል]። አሁንም [ፈቃድ] ይገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አዎንታዊ ምላሽ እንደሚጠብቁ ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል።
በትግራይ ለማካሄድ የታቀደው የምክክር ሂደት እስኪሳካ ድረስ በእቅድ የተያዘው፤ በቀጣዩ ሳምንት “ከፍተኛ ጥሪ” በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የምክረ-ሐሳብ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ማካሄድ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህ መርሃ ግብር የሚሳተፉት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች እና ከትግራይ ክልል የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች እንደሆኑም አስረድተዋል።
“እኛ ውሳኔያችን ዞሮ ዞሮ አጀንዳውን ከትግራይ መውሰድ ነው። ተሳታፊዎቹ በትግራይ ከወረዳ ጀምሮ ያሉ ስለሆነ። ነገር ግን ያ እስኪስተካከል እና ጊዜዎች፣ ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ለጊዜው ዝም ብሎ ከመቀመጥ፤ አንደኛ ዋናው እና ትልቁ ሥራ ምክረ ሐሳብ መውሰድ ነው። በቀጣይነት ምን እናድርግ የሚለውን እነሱ የሚሉንን ለመስማት እና ምክረ ሐሳባቸውን ለመውሰድ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ስለ መርሃ ግብሩ ዓላማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
በዚህ መርሃ ግብር “ሁኔታዎች በሚመቻቹበት ጊዜ ትግራይ ላይ ምክክሩ እንዴት ነው ሊካሄድ የሚችለው?” በሚለው እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ንግግር እንደሚኖር አስረድተዋል። በቀጣይነት በመቐለ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዞን ዋና ከተሞችም ሂደቱ “በምን አይነት ሁኔታ ይከናወናል?” የሚለው የሚታይ እንጂ፤ “ትግራይ ላይ የሚደረገው ምክክር ይቀራል” ማለት እንዳልሆነም ፕሮፌሰር መስፍን አስረድተዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ የትግራይ ክልል አጀንዳዎች የሚሰባሰቡበትን መድረክ በአዲስ አበባ ለማካሄድ በአማራጭነት መያዙን ተናግረው ነበር። ኮሚሽኑ ሌሎች አማራጮችን የሚከተለው፤ በትግራይ ክልል ምክክሩን ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ “በትክክል አለ ወይስ በፍጹም ተዘግቷል” በሚለው ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር ከተነጋገረ በኋላ እንደሆነም በወቅቱ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























