ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የግማሽ ቢሊዮን ዶላር ጨረታ በድጋሚ አወጣ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግማሽ ቢሊዮን ዶላር ልዩ የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጨረታ በነገው እለት ሊያካሄድ መሆኑን አስታወቀ። ባንኩ ተመሳሳይ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ለልዩ ጨረታ ሲያቀርብ፤ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው ነው።

ባንኩ ዛሬ አርብ የካቲት 13፤ 2018 ባወጣው መግለጫ፤ ፍላጎት ያላቸው ባንኮች ነገ ከረፋዱ አራት ሰዓት እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የጨረታ ሰነድ በማስገባት መሳተፍ እንደሚችሉ አስታውቋል። የጨረታው ውጤት በተመሳሳይ ቀን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይፋ እንደሚደረግም ባንኩ ገልጿል።

ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ጥር 19፤ 2018 በተመሳሳይ ሁኔታ አውጥቶት በነበረው የግማሽ ቢሊዮን ዶላር ልዩ የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጨረታ የንግድ ባንኮች ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተው ነበር። በዚህ ጨረታ 31 ባንኮች የተሳተፉ ሲሆን፤ የዶላር ፍላጎቱም ከአቅርቦቱ በ92.3 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ነበረው።

በወቅቱ ለአንድ ዶላር የቀረበው ከፍተኛ ተመን 154.99 ብር ሲሆን፤ ዝቅተኛው ደግሞ 153.5 ብር መሆኑን ባንኩ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ብሔራዊ ባንክ ከሶስት ቀናት በፊት ባካሄደው 18ኛ ዙር መደበኛ ጨረታ፤ ለአንድ ዶላር በቀረቡት ከፍተኛ እና ዝቅተኛ ተመኖች መካከል ያለው ልዩነት እጅግ የጠበበ ሆኗል። 

ሰባ ሚሊዮን ዶላር ለቀረበበት ለዚህ ዙር ጨረታ የተሰጠው ከፍተኛ ዋጋ 155.12 ብር ሲሆን፤ ዝቅተኛው ደግሞ 155.10 ብር ነበር። በዚህ ጨረታ ላይ የተሳተፉ 31 ባንኮች ያሳዩት የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት፤ ብሔራዊ ባንክ ካቀረበው ከእጥፍ በላይ የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሚካሄዱት የብሔራዊ ባንክ ጨረታዎች፤ የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ከአቅርቦቱ በከፍተኛ ሁኔታ መብለጥ እያሳየ ይገኛል። የባንኮች ፍላጎት በ75.31 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ባሳየበት በማክሰኞው ጨረታ፤ ዶላር ማግኘት የቻሉት ሃያ አንዱ ብቻ ናቸው።

ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት ልዩነት “መደበኛ” እና “ተከታታይ” የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጨረታ ማካሄድ የጀመረው ከመጋቢት 2017 ዓ.ም መጨረሻ አንስቶ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)