የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሙሉ ለመሉ በበይነ መረብ ለመስጠት መታቀዱ፤ የፍትሃዊነት እና የተፈጻሚነት ጥያቄ በፓርላማ አስነሳ 

ዘንድሮ የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት መታቀዱ፤ የመሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች ባሉ ተማሪዎች ውጤት ላይ “ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ” ሊኖረው እንደሚችል የፓርላማ አባላት ስጋታቸውን ገለጹ። ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ 122 ሺህ የመፈተኛ ኮምፒውተሮች መዘጋጀታቸውን እና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል የተለያዩ የመንግስት አካላትን የያዘ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጿል።

ይህ የተገለጸው የትምህርት ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 7፤ 2018 ባቀረበበት ወቅት ነው። የተቋሙን የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው በንባብ ያቀረቡት፤ በሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እሸቱ ገላዬ ናቸው።

አቶ እሸቱ በዚሁ ሪፖርታቸው በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመደበኛ እና በድጋሚ የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት 554,965 መሆናቸውን ተናግረዋል። የዘንድሮውን ሀገር አቀፍ ፈተና “መቶ በመቶ በበይነ መረብ (online) ለመስጠት” ከክልል ፕሬዝዳንቶች እና ከትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ስራዎችን ሲከናወኑ መቆየታቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት በመጀመሪያ ያቀደው በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ነበር። መስሪያ ቤቱ በወቅቱ ባደረገው ዳሰሳ፤ ለፈተናው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ግዢ ለማከናወን እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ መገንዘቡን የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዛሬው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

ለመፈተኛ መሳሪያዎች የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን በውጭ እርዳታ ለመሸፈን ቢታስብም፤ በጊዜው የታሰበውን ያህል እንዳልተገኘ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የ12ኛ ክፍል ፈተናን በበይነ መረብ መስጠት “ኩረጃን ለመከላከል” ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብሎ የሚያምነው ትምህርት ሚኒስቴር፤ ለጥቂት ተማሪዎች በኦንላይን የመጀመሪያውን ፈተና የሰጠው በ2016 ዓ.ም. ነበር።

በዚህ ወቅት ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ስምንት በመቶ ወይም 29,736 የሚሆኑት በበይነ መረብ የተፈተኑ ነበሩ። ሚኒስቴሩ ይህንን የተማሪዎች ቁጥር በቀጣዩ ዓመት ወደ 150 ሺህ ለማሳደግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በበይነ መረብ መፈተን የቻለው 134,570 ተማሪዎችን ብቻ ነበር። 

ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በወረቀት እና በበይነ መረብ ሲሰጥ የቆየው የ12ኛ ክፍል ፈተና፤ ዘንድሮ “መቶ በመቶ” በኦንላይን እንዲካሄድ መታቀዱ በፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ጥያቄዎችን አስነስቷል። በዛሬው ስብሰባ ላይ የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄዎች በንባብ ያቀረቡት አቶ ታደሰ ጌጡ፤ ፈተናውን በበይነ መረብ ለመስጠት መታቀዱ መልካም መሆኑንም በመንደርደሪያነት ጠቅሰዋል። 

ሆኖም ፈተናው በዚህ መልክ መሰጠቱ፤ የኮምፒውተር፣ የመብራት እና የኔትወርክ መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው ትምህርት ቤቶች የሚፈተኑ ተማሪዎች ውጤት ላይ “ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ” ሊኖረው እንደሚችል የፓርላማ አባሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። አቶ ታደሰ ይህን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ምን መፍትሔ እንዳለውም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። 

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በምላሻቸው፤ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት 122 ሺህ ኮምፒውተሮች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ፈተናው ከመሰጠቱ ቢያንስ ሁለት ወር አስቀድሞ የሙከራ ፈተናዎች (mock exam) ለተማሪዎች እንደሚሰጡም አመልክተዋል። 

“ሁሉም ተማሪዎች ገብተው፣ ከፈተናው ጋር ተለማምደው፣ ፈተናውን እንዲወስዱ፣ ፈተና መመለስ እንዲችሉ፣ ስልጠና [እንሰጣለን]። ቀጣይነት ያለው ልምምድ አድርገው ነው የሚገቡት። ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚል እምነት የለንም” ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባሉ ለቀረበው ስጋት ምላሽ ሰጥተዋል።

በበይነ መረብ ሙሉ ለሙሉ ፈተና የመስጠት ሂደቱ አዲስ ነገር በመሆኑ “የሚጎረብጡ ነገሮች ሊኖሩ” የተቀበሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ነገር ግን የፓርላማ አባሉ ያነሷቸውን የመሰሉ ተግዳሮቶች ወደፊት ለመራመድ “እንዲከለክሉን ልንፈቅድላቸው አይገባም” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል። ተፈታኞቹን አስቀድሞ ለማዘጋጀት እና እንዳይጎዱ ለማድረግ “በተቻለ መጠን” ጥረት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

በአንዳንድ ቦታዎች የእጅ ስልክ ያላቸው ተፈታኞች የፈተናውን ሂደት “መለማመድ” መጀመራቸውንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቁመዋል። “ኔትወርክ የሌለባቸው ቦታዎች እስክናስተካክል ካልሆነ በቀር፤ ቢያንስ ለአንድ ወር፣ ለአንድ ወር ተኩል በተከታታይ እንዲለማመዱ እናደርጋለን” ሲሉም ሚኒስትሩ አክለዋል። 

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ከበደ በበኩላቸው የ12ኛ ክፍል ፈተናን በበይነ መረብ ከመስጠት ጋር ተያይዞ አራት ዋና ችግሮች እንዳሉ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት አስረድተዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም በዝርዝር አብራርተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በመጀመሪያነት ያነሱት ችግር የመብራት መቆራረጥ ችግርን ነው። ለዚህ ችግር ምላሽ ለመስጠት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በትምህርት ሚኒስትሩ የሚመራ የጋራ ግብረ-ኃይል በፌደራል፣ በክልል እና በዞን ደረጃ መቋቋሙን ዶ/ር እሸቱ ገልጸዋል።

አንድ የመፈተኛ ማዕከል የ12ኛ ክፍልን ፈተና መስጠት የሚችለው፤ “የሚሰራ መሆኑ በሙከራ የተረጋገጠ” ጄነሬተር እንዳለው “ተፈትሾ ሲረጋገጥ” ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ በሁለተኛነት ላነሱት የኢንተርኔት አገልግሎት ችግርም በተመሳሳይ  በየደረጃው በተቋቋሙ ግብረ-ኃይሎች አማካኝነት ከኢትዮ ቴሌኮም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።

በመፈተኛ ማዕከላቱ የሚገኙ እያንዳንዳቸው ኮምፒውተሮች ከኔትወርክ ጋር መገናኘታቸው እና ፈተና ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውም በሙከራ እንደሚረጋገጥ ዶ/ር እሸቱ አክለዋል። ይህን ሁሉ ዝግጅት ተደርጎ ከአቅም በላይ የሆኑ ሰው ሰራሽም ሆኑ ቴክኒካዊ ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለእነዚህም ቢሆን “ፈጣን ምላሽ ሰጪ ግብረ-ኃይል” በየደረጃው መቋቋሙን ገልጸዋል።

“በደቂቃዎች ውስጥ በሰዓታት ውስጥ ፈተናውን መልሰን ማስጀመር የምንችልበት ደረጃ ላይ [ነን]። ምላሽ የሚሰጡ በየደረጃው ተቋቁመዋል። ይሄም የማይሆን ከሆነ ደግሞ መጠባበቂያ እቅድ (backup plan) አዘጋጅተናል። ‘እኛ መቶ ፐርሰንት እናደርጋለን ስለዚህ የሚመጣ ነገር አይኖርም’ በሚል ብቻ አይደለም፤ ዝርዝር እቅዶች አሉን” ሲሉ ዶ/ር እሸቱ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።  

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ በዲጂታል ዕውቀት (digital literacy) ሊያጋጥሙ የሚችሉ የግንዛቤ ውስነቶችንም እንደ አንድ ችግር ጠቅሰዋል። ይህ ችግር በተማሪዎች እና በፈተና አስፈጻሚዎች ሊኖር እንደሚችል ያመኑት ዶ/ር እሸቱ፤ ይህንን ችግር ለመፍታት “ከፍተኛ በጀት ወጥቶ እና ጊዜ ተወስዶ” ስለ ሲስተሙ ለፈተና አስፈጻሚዎች የተግባር ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ይህንንኑ እንዲደግፉ አንድ ወይም ሁለት ለICT “የቀረበ” የትምህርት ዝግጅት ያላቸው የፈተና አስፈጻሚዎች የመመደብ ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ፈተናው በበይነ መረብ በተሰጠበት ወቅት የቴክኖሎጂ ፍርሃት (technophobia) ያጋጠማቸው ጥቂት ተማሪዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ዶ/ር እሸቱ፤ ለእነዚህ ተማሪዎች እና የእይታ ችግር ላለባቸው ተፈታኞች “ልዩ ረዳት” ለመመደብ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ በሰጧቸው ማብራሪያዎች ማስተማመኛ ለመስጠት ቢሞክሩም፤ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ግን የ12ኛ ክፍል ፈተናን በመስጠት ረገድ የተመለከቷቸውን ክፍተቶችን በማንሳት በድጋሚ ጥያቄውን ሰንዝረዋል። 

የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናውን “ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ እሰጣለሁ” ማለቱን ተከትሎ፤ “ኮምፒውተር ፍለጋ የሚሯሯጡ እና እርዳታ የሚጠይቁ” የትምህርት ተቋማት በየወረዳው መኖራቸውን ዶ/ር ነገሪ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። የመሰረተ ልማት አቅርቦት የሌለባቸው እና መብራት “አንድ ወር ተቋርጦ” የሚቆይባቸው ወረዳዎች እንዳሉ የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ፤ በተመሳሳይ ኔትወርክ የሚቆራረጥበት ሁኔታ እንዳለ አንስተዋል።  

“የታብሌት ግዢ በተመለከተ ካልሆነ እዚሁ በማምረት [እንወጣዋለን] የተባለበትን እናስታውሳለን። ምን ስለሰራን ነው መቶ በመቶ ፈተናውን [የምንሰጠው]? አዲስ አበባ ያሉትን አይደለም። አዳማ፣ ባህርዳር እና ሌሎች ትልልቅ ከተሞች ላይ ያሉትን አይደለም። የእኛ ትልቅ ስጋት ወደ ወረዳዎች ስንሄድ ያለውን ሁኔታ ነው” ሲሉ ዶ/ር ነገሪ ተናግረዋል።  

“ወደ ወረዳዎች ወርደን አይተናል ወይ? በደንብ አጥንተን ነው? ወደ ምንፈልገው ደረጃ ዝግጅት እንዲያደርጉ ምን እገዛ አድርገን ነው ወደዚህ ምንሄደው? ‘ጥሩ ነው እንገፋበታለን’ ከተባለ ደግሞ ምናልባት መተንበይ የማይቻሉ (unpredictable)  የሆኑ ችግሮች ቢፈጠሩ ምን መጠባበቂያ (backup) አላችሁ?” ሲሉ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎችን በድጋሚ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የፓርላማው “ፍርሃት እና ጭንቀት እኛም ጋር አለ” በማለት ስጋቱን እንደሚጋሩ ገልጸዋል። እርሳቸው የሚመሩት የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥን የሚከታተል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመ ግብረ ኃይል እንዳለ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ይህ አካል ለሚከናወኑ ስራዎች በዝርዝር ጊዜ በማስቀመጥ፣ መቼ ማለቅ እንዳለባቸው የሚከታተል መሆኑን አስረድተዋል። 

ይህ ግብረ ኃይል ከትምህርት ሚኒስቴር በተጨማሪ የክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በአባልነት የያዘ እንደሆነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። ለስራው አጋዥ የሚሆን የቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋሙንም አክለዋል። 

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት ከመታቀዱ በፊት፤ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ ምን ያህል ኮምፒውተሮች እና ታብሌቶች እንዳሉ የመቁጠር ተግባር አስቀድሞ መከናወኑን የትምህርት ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት 122 ሺህ የሚሆኑ የመፈተኛ መሳሪያዎች እንዳሉ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ያሉ ተጨማሪ ስድስት ሺህ መሳሪያዎችን አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ ለማስቀመጥ መታቀዱን ተናግረዋል። 

“እነዚህ 122 ሺህ ኮምፒውተሮች ያሉበትን ቦታ በሙሉ አይተን፤ ‘ምን ያህሉ የቴሌ ኮኔክሽን ይቀረዋል? ምን ያህሉ የመብራት ችግር አለበት?’ ብለን በዝርዝር እያንዳንዱን [እያየን ነው]። ሁሉም ትምህርት ቤቶች መፈተኛ ጣቢያ ይሆናሉ ማለት አይደለም። የመፈተኛ ጣቢያዎችን በዝርዝር እየሄድንበት ነው” ብለዋል።

“እኛም ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ ሳንሆን፣ ‘መቶ በመቶ [ፈተናውን] እንሰጣለን’ ብለን ያለ Plan B አንሰራም። በተወሰነ ደረጃ Plan B ይዘን፣ በወረቀት የሚፈተኑ ቢኖሩ ብለን፣ እነኛን ነገሮች ቴስት አድርገን ከጨረስን በኋላ የሚቀሩ ካሉ እንዴት እንደምንፈትን እየተዘጋጀን ነው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)