ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ ክልል ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ የተመረጠው የክልሉ ምክር ቤት “ወደ ስራ እንዲመለስ” ውሳኔ አስተላለፈ። ፓርቲው የትግራይ መንግስት አስፈጻሚ አካል፤ “ሁሉንም አቅሞች ያካተተ” እና “አቃፊ” ሆኖ እንዲቋቋም ወስኗል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅናው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የተሰረዘው ህወሓት ውሳኔዎቹን ያስተላለፈው፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው ነው። ካለፈው ረቡዕ ሚያዝያ 7፤ 2018 ጀምሮ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፤ “በፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም” ላይ እንዲሁም “በወቅታዊ ሁኔታዎች” ላይ “በጥልቀት እና በስፋት” መወያየቱን ፓርቲው ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይህ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተካሄደው፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን፤ በድጋሚ ከተራዘመ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ላለፈው አንድ ዓመት ሲመሩ የቆዩትን የሌፍተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደን የስልጣን ዘመን ያራዘሙት፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2015 ዓ.ም. የወጣን ደንብ እና ሌሎች ህጎችን በመጥቀስ ነበር።
ህወሓት በዛሬው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት የወጣን ህግ በመጥቀስ” የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን የቆይታ ጊዜ ከፓርቲው “እውቅና እና ተሳትፎ ውጭ”፣ “በነጠላ ውሳኔ ማራዘሙን በይፋ ገልጿል” ሲል ወንጅሏል። በዚህ መሰረት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ “ስለ ሰላም ተብሎ ተገትቶ ቆይቷል” ያለውን የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ስራ”፤ ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ መወሰኑን አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ህዝብ “የሉዓላዊ ስልጣን እና ወሳኝነት” መገለጫ” መሆኑን የጠቀሰው ህወሓት፤ “ወደ 2.8 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የመረጠው” መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል። ህወሓት ይህን ቢልም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጳጉሜ 2014 ዓ.ም. ከተካሄደው የትግራይ ክልል ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ባካሄደው ስብሰባ፤ ምርጫው “እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና እና ተፈጻሚነት የሌለው ነው” ሲል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በዛሬው መግለጫው የትግራይ ህዝብ “በመረጠው መንግስት የመተዳደር መብቱ”፤ “ለረጅም ጊዜ የታገለለት”፣ “ውድ ዋጋ የከፈለበት” እና “የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበት” እንደሆነ ገልጿል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ የትግራይ መንግስት አስፈጻሚ አካል “ሁሉንም አቅሞች ያካተተ” እና “አቃፊ” ሆኖ እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉንም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































