የአውሮፕላን መንገደኞች የአቪዬሽን ደህንነት ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስገድደው አዋጅ ጸደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 13፤ 2018 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የአውሮፕላን መንገደኞች የአቪዬሽን ደህንነት ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስገድደውን አዋጅ በሁለት ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ገቢ ይደረጋል የተባለው ይህ ክፍያ፤ በፓርላማ አባላት ጥያቄ ተነስቶበታል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተመራጩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ የአውሮፕላን መንገደኞች ለአቪዬሽን ደህንነት ክፍያ ክፈሉ መባሉ “መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት” አለበት ከሚለው ጽንሰ ሀሳብ ጋር የሚቃረን መሆኑን ተናግረዋል። የሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት ክፍያን ሊከፍሉ የሚገባው አየር መንገዶች እንጂ መንገደኞች ሊሆኑ እንደማይገባም የፓርላማ አባሉ አሳስበዋል። 

“የሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ ለብሔራዊ ደህንነት ገቢ ይደረጋል መባሉ የሀገሪቱን የገንዘብ ስርዓት አለማወቅ ነው። ለሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንም ለብሔራዊ ደህንነትም በጀት የሚመድበው ፓርላማው ሆኖ እያለ የመንግስትን የፋይናንስ ስርዓትን የሚጥስ በመሆኑ ይህ አንቀጽ መስተካከል አለበት” ሲሉ ዶ/ር ደሳለኝ በአዋጁ ላይ የማሻሻያ ሃሳብ አቅርበዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ወዳጆ በበኩላቸው ክፍያ እንዲሰበስቡ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው የገንዘብ ሚኒስቴር እና ገቢዎች ሚኒስቴር መሆናቸውን አስታውሰዋል። እነዚህ ተቋማት እያሉ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ገንዘብ እንዲሰበስብ በአዋጅ ረቂቅ ላይ መጠቀሱን ያነሱት አቶ ደሳለኝ፤ ይህ በምን አግባብ እንደሚፈጸም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። 

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት በፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ፈትሂ ማህዲ፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ገንዘብ መሰብሰብ እንደሚችል በህግ እንደተፈቀደለት አስረድተዋል። ለመስሪያ ቤቱ ይህን ፈቃድ የሰጠው፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በ2014 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

“በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ደህንነቶችን ለማስከበር ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ደግሞ በመንግስት በጀት ብቻ የሚቻል አይደለም” ያሉት ዶ/ር ፈትሂ፤ ለዚህ ተግባር ሌሎች ሀገራትም ክፍያዎች እንደሚጠይቁ አስገንዝበዋል። ታንዛኒያ ለአቪዬሽን ደህንነት አገልግሎት የሚውል በአንድ ተሳፋሪ ከሁለት እስከ አምስት ዶላር እንደምታስከፍልም በምሳሌነት አንስተዋል። 

ይህ አሰራር “ከዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አሰራር ጋር የሚስማማ ነው” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ፤ በኢትዮጵያም ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል። በዚህ መሰረት የሀገር ውስጥ መንገደኞች በእያንዳንዱ በረራ 30 ብር፣ ዓለም አቀፍ መንገደኞች ደግሞ አንድ ዶላር እየከፈሉ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፈትሂ፤ በአዲሱ አዋጅ የተካተተው ድንጋጌ ይህንን አሰራር ህጋዊ ለማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል። 

ድንጋጌውን የያዘው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት ማሻሻያ የአዋጅ ረቂቅ ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ለፓርላማ በቀረበበት ወቅት፤ ውይይት ሳይካሄድበት እና አስተያየትም ሆነ ጥያቄ ሳይቀርብበት ነበር ጉዳዩን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራው። በዋነኛነት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሥልጣን እና ተግባራት ላይ ማሻሻያዎችን ያደረገው ይህ አዋጅ፤ ተመሳሳይ ስያሜ በመያዝ ከ20 ዓመት በላይ በስራ ላይ የቆየውን አዋጅ የተካ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)