በነዳጅ የሚሰሩ 1,200 አውቶብሶችን ወደ ጋዝ ተጠቃሚነት ለመቀየር 1.4 ቢሊዮን ብር በጀት ያስፈልጋል ተባለ 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ፣ በነዳጅ የሚሰሩ 1,200 የህዝብ ማመለሻ አውቶብሶችን ሞተር፤ በኢትዮጵያ መመረት የጀመረውን የተፈጥሮ ጋዝ እንዲጠቀሙ ለመቀየር 1.4 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልግ የከተማይቱ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ። በመዲናይቱ የሚገኙ አውቶብሶችን ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተጠቃሚነት የመቀየር ሙከራ መጀመሩንም ቢሮው አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ይህን ያስታወቁት፤ ዛሬ አርብ ሚያዝያ 30፤ 2018 በተካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ባካሄደው ጉባኤ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ነው። በአሁኑ ወቅት ያለው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት የተመለከቱ ጉዳዮችን በማብራራያቸው ያነሱት አቶ ያብባል፤ ለዚህ ችግር በመፍትሔነት ከተቀመጡት ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ማበራከት እንደሆነ አስረድተዋል።

በሶማሌ ክልል በሚገኘው የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት አማካኝነት ኢትዮጵያ የጋዝ ምርት ባለቤት መሆን መጀመሯን የጠቆሙት አቶ ያብባል፤ ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የከተማ አውቶብሶችን ወደ ጋዝ ሞተር የመቀየር አቅጣጫ” ማስቀመጣቸውን አስታውሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ አሰራር ተግባራዊ እንዲደረግ መመሪያ የሰጡት፤ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክቱን ባለፈው መስከረም ወር በመረቁበት ወቅት ነበር።

“በዚህ አመት ቢበዛ በአንድ አመት ውስጥ 2,000 የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ አውቶብሶች፤ አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን” ያሉት አብይ፤ ይህም የትራንስፖርት ዋጋን ቢያንስ በሚቀጥለው አመት ቢያንስ በ50 በመቶ መቀነስ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረው ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ በዛሬው ማብራሪያቸው፤ አውቶብሶችን ወደ ጋዝ የመቀየር ሙከራ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።

“እንደከተማ 1,200 የሚሆኑትን፣ ቀድመው ያሉትን የከተማ የነዳጅ አውቶብሶች፣ ወደ ጋዝ ሞተር የመቀየር እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የጋዝ ስቴሽኑን ቃሊቲ ዲፖ ገንብተን አጠናቀናል። ከዚህ በተጨማሪም ሁለት አውቶብሶች ላይ የሞተር ገጠማ ተደርጓል። ይሄም ሙከራ እየተካሄደ ነው ያለው። ይህ ሙከራ ሲጠናቀቅ 1,200 አውቶብሶችን ወደ ጋዝ የምንቀይር ይሆናል” ሲሉ የቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል። 

የእነዚህን አውቶብሶች ሞተር ከነዳጅ ወደ ጋዝ ለመቀየር 1.4 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልግም አቶ ያብባል ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራውን አንገብጋቢነት “ታሳቢ በማድረግ”፤ ለቅድሚያ ክፍያ የሚያስፈልገውን ከ273 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ በመፈጸሙን ስራው መጀመሩን የቢሮ ኃላፊው አመልክተዋል።

ቤንዚን እና ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን የተፈጥሮ ጋዝ በሚጠቀሙ መኪናዎች የመተካቱን አስፈላጊነት፤ የገንዘብ ሚኒስቴርም ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ሆኗል። ሚኒስቴሩ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ባወጣው መመሪያ፤ በቤንዚን እና በናፍጣ የሚሰሩ የጭነት እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ማሳሰቡ ይታወሳል።

ይህ ገደብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በሌሎች ተቋማት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተፈቀደላቸውን እና በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን እንደማይመለከትም በወቅቱ ገልጿል። የገንዝብ ሚኒስቴር በዚሁ መመሪያው፤ “ሙሉ ለሙሉ” በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማንኛውም ዓይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፤ ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ሆነው እንዲገቡ ፈቅዷል። 

ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ መመረት የጀመረው የተፈጥሮ ጋዝ ይቀርብላቸዋል ተብሏል።በሶማሌ ክልል የሚገኘው የመጀመሪያው ዙር የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፕሮጀክቱን በመረቁበት ወቅት ተናግረው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ 1.33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር ማስጀመራቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)