ለጋምቤላ ክልል የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት በአዲስ መልክ የተዘጋጀ የደንብ ልብስ፤ ከደቡብ ሱዳን ሰንደቅ ዓላማ ጋር የሚመሳሰል ባንዲራ በመያዙ ማስተካከያ እንዲደረግበት ትዕዛዝ ተላለፈ። ትዕዛዙን ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ለአባላቱ ያስተላለፈው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ነው።
የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት ይጠቀሙበት የነበረው የደንብ ልብስ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ውሳኔ ያሳለፈው፤ በክልሉ ከወራት በፊት የነበረውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ነው። ከአንድ ወር በፊት ለተላለፈው ለዚህ ውሳኔ ምክንያት የሆነው፤ የቀድሞውን የደንብ ልብስ የሚጠቀሙ “ጽንፈኛ ቡድኖች” በመንገዶች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ በመገኘታቸው እንደሆነ አንድ ኮሚሽኑ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት እንዲመሩ ባለፈው ወር የተሾሙት አቶ ዶሮ ካሩ፤ አዲሱ የደንብ ልብስ የተዘጋጀው የአድማ ብተና አባላቱን ከሌሎች የፖሊስ አባላት ለመለየት እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአርባ ምንጭ ከተማ በሚገኝ የልብስ ስፌት ፋብሪካ የተመረተው አዲሱ የደንብ ልብስ ጋምቤላ የደረሰው ከአንድ ሳምንት በፊት እንደነበርም አመልክተዋል።

በወቅቱ እርሳቸው ለስራ ሰንዳፋ ከተማ እንደነበሩ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ጉዳዩን ምክትላቸው ሲከታተሉ እንደነበርም አስረድተዋል። “በስራ መደራረብ” ምክንያት መዘግየቱ የተገለጸው አዲሱን የደንብ ልብሱን የማከፋፈል ሂደት፤ የተጀመረው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር።
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከትላንት በስቲያ ባወጣው ማስታወቂያ፤ የቀድሞውን የአድማ ብተና የደንብ ልብስ የያዙ አባላት ከቅዳሜ ግንቦት 15፤ 2018 ጀምሮ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገቢ እንዲያደርጉ “ጥብቅ” ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር። ኮሚሽኑ ይህን ማሳሰቢያ ካሰራጨ ከሰዓታት በኋላ ባወጣው ሌላ ማስታወቂያ፤ በአዲሱ የደንብ ልብስ ላይ “የሰንደቅ ዓላማ አቀማመጥ ስህተት መከሰቱን” አምኗል።
የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የባንዲራ አቀማመጥ ስህተቱን የፈጠረው አርባ ምንጭ የሚገኝ ፋብሪካ እንደሆነ እና ስህተቱም በሁሉም የደንብ ልብሶች ላይ ማጋጠሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ኮሚሽነሩ የደንብ ልብሶቹ ብዛት 300 እንደሆነ ቢገልጹም፤ ስህተቱን ስለሰራው ድርጅት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሌላ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊ በበኩላቸው፤ በአዲሱ የደንብ ልብስ ላይ የተፈጠረው የሰንደቅ ዓላማ ስህተት መነሻው “የቀለማት ቅደም ተከተል መዛባት” እንደሆነ አስረድተዋል። በጋምቤላ ሰንደቅ ዓላማ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ሊቀመጥ ይገባ የነበረው “ቀይ” ቀለም በስህተት “ጥቁር” ሆኖ እንዲሰፋ መደረጉ፤ ባንዲራው ከደቡብ ሱዳን ባንዲራ ጋር እንዲመሳሰል ማድረጉንም አብራርተዋል።
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ስህተቱ “በስፌት በቀላሉ የሚስተካከል” እንደሆነ ከትላንት በስቲያ ባወጣው ማስታወቂያ ላይ ጠቁሟል። ኮሚሽኑ በዚሁ ማስታወቂያው እያንዳንዱ የአድማ ብተና ፖሊስ አባል “በግል” ወይም “ኮሚሽኑ ወደ አዘጋጀው የልብስ ሰፊ ዘንድ በመሄድ” በደንብ ልብሱ ላይ “በአፋጣኝ ማስተካከያ እንዲያደርጉ” ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በጋምቤላ ክልል ባለፉት ወራት የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ፤ የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት “የታጠቁትን የጦር መሳሪያ ገቢ እንዲያደርጉ” እና “የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ” ተመሳሳይ ትዕዛዝ ተላልፎላቸው እንደነበር ይታወሳል። የክልሉ መንግስት ያቀረበውን ይህንን ጥሪ ያልተቀበሉ የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት “በጥፋተኛነት መለየታቸውን” የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፈው መጋቢት ወር አስታውቆ ነበር።

አዲሱን የደንብ ልብስ የተመለከተ ትዕዛዝ የተላለፈላቸው የአድማ ብተና አባላት፤ ከትላንት ጀምሮ የተፈጠረውን ስህተት በልብስ ሰፊ እያስተካከሉ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የደንብ ልብሳቸው በዚህ ምልክት የተስተካከለላቸው የፖሊስ አባላትም ወደ ምድብ ስራቸው መመለሳቸውን አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































