በተስፋለም ወልደየስ
መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲከፋፈል በዚህ አመት ከመደበው 98 ሚሊዮን ብር ውስጥ፤ የተወሰነው መጠን በሚቀጥለው ሳምንት ለፖለቲካ ፓርቲዎች መከፋፈል ሊጀመር ነው። ለፓርቲዎች የሚሰጠው ገንዘብ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት እንዲከፋፈል በቀመር አማካኝነት የተደለደለ ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተዘጋጀው የክፍፍል ቀመር መሰረት መንግስት ለፓርቲዎች ከሚመድበው ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶ ያህሉ፤ በቦርዱ ዕውቅና ተሰጥቷቸው ለሚንቀሳቀሱ ለሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት ይከፋፈላል። የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ቅዳሜ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ “የገንዘብ ድጋፍ ከምርጫ ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም”።
“መንግስት፤ ፓርቲዎች የህዝብ ፍላጎት aggregate እያደረጉ፣ ወደ አማራጭና ወደ ፖሊሲ ለሚቀይሩ ፓርቲዎች ሁልጊዜም ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለበት” ብለዋል ሰብሳቢዋ። “በእኩልነት መርህ ላይ ተመስርቶ በሚከፋፈለው ገንዘብ ላይ ህጋዊ ዕውቅና ያላቸው ፓርቲዎች በሙሉ ተካፋይ ይሆኑበታል” ሲሉም አክለዋል።
የቦርድ ሰብሳቢዋ ለዚህ አባባላቸው በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የአረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲን በምሳሌነት አንስተዋል። “ለምሳሌ አረና አሁን [በምርጫ] እየተሳተፈ አይደለም። ግን ህጋዊ ፓርቲ ነው። እንቅስቃሴዎች እዚህም እዚያም ያደርጋል። ሌሎችም ፓርቲዎች እንደዚያው ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ቦርዱ የገንዘብ ክፍፍሉን ለመፈጸም የሚያስችለውን “የማመልከቻ ቅጽና የግዴታ ፎርም” ዛሬ ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አከፋፍሏል። ፓርቲዎቹ ማመልከቻዎቻቸውን ሞልተው ለቦርዱ ሲያቀርቡ፤ የመጀመሪያው ዙር የገንዘብ ክፍፍል እንደሚፈጸም በዛሬው ስብሰባ ላይ ተገልጿል። አመቱ የምርጫ ዘመን በመሆኑ ምክንያት፤ ቦርዱ ሁለተኛውን ዙር የገንዘብ ክፍፍል ለማድረግ “ሌላ ሶስት እና አራት ወራት” እንደማይጠብቁ የቦርድ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ለፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት የሚመደበው የገንዘብ ድጋፍ በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ እንደመጣ መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግስት ባለፈው ዓመት ለተመሳሳይ ዓላማ የመደበው በጀት 60 ሚሊዮን ብር ነበር። ከዓመታት በፊት ፓርቲዎች ያገኙት የነበረው ድጋፍ 30 ሚሊዮን ብር እንደነበር በዛሬው ስብሰባ ላይ ተጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)