ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ወደ መቐለ በረራ ያደረገ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን፤ በአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ በሚገኝ የኮሚኒኬሽን መሳሪያ ብልሽት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ለማረፍ መገደዱን አንድ የአየር መንገዱ ኃላፊ እና መንገደኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። መንገደኞቹ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ በዚያው አውሮፕላን መቐለ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ እና ነገ ወደ መቐለ ለማድርግ ያቀዳቸው በረራዎች ብዛት ስድስት ነው። የአየር መንገዱ ለዛሬው የመጀመሪያ በረራው የመደበው አውሮፕላን ጠዋት 12 ሰዓት ከሩብ ከአዲስ አበባ ተነስቶ አንድ ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ መቐለ እንዲያርፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ነበር።
በዚህ በረራ የተጓዙ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ መንገደኛ፤ የተሳፈሩበት አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ጠዋት 12 ሰዓት ተኩል ተነስቶ መቐለ ለሁለት ሰዓት ሩብ ጉዳይ መድረሱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል። አውሮፕላኑ በመቐለ ሳያርፍ ወደ አዲስ አበባ መመለሱን የገለጹት መንገደኛው፤ በጉዞ ላይ እያሉ አብራሪው “በመቐለ ያሉ መሳሪያዎች ላይ የብልሽት ችግር ስላጋጠመ” እየተመለሱ መሆኑን እንደነገራቸው አስረድተዋል።

በጠዋቱ በረራ ወደ መቐለ የሚመጣ መንገደኛን ለመቀበል በአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ተገኝቶ እንደነበር የገለጸ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ወደ አየር ማረፊያው ሲጠጋ መመልከቱን ገልጿል። አውሮፕላኑ በሰላም አርፏል ብለው የገመቱ እርሱ እና ሌሎች ተቀባዮች፤ መንገደኞች ከአየር ማረፊያው እስኪወጡ ሲጠብቁ መቆየታቸውንም ተናግሯል።
መንገደኞቹ በመዘግየታቸው የሚቀበለው ግለሰብ ስልክ ላይ ደጋግሞ ደውሎ ባለመስራቱ፤ አጭር የጹሁፍ መልዕክት በመላክ ምላሹን ሲጠብቅ እንደነበር የመቐለው ነዋሪ አመልክቷል። ከቆይታ በኋላ በቴክኒክ ችግር ምክንያት አውሮፕላኑ ተመልሶ አዲስ አበባ ማረፉን የሚገልጽ መልዕክት ከመንገደኞች እንደደረሳቸው ነዋሪው ጨምሮ ገልጿል።
በጠዋቱ በረራ የተጓዙት መንገደኛ፤ አውሮፕላኑ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ እርሳቸው እና ሌሎች መንገደኞች ለሰዓታት ከአውሮፕላኑ ሳይወርዱ ለመቆየት እንደተገደዱ ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ በተጓዦች ዘንድ ድንጋጤ ፈጥሮ እንደነበረም አልሸሸጉም።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ጦርነት ወዲህ የአውሮፕላን በረራ መዘግየት እና መሰረዝ፤ በነዋሪዎች ዘንድ እንደ አጋጣሚ ክስተት ብቻ አይቆጠርም። የመቐለ፣ የአክሱም እና የሽረ ነዋሪዎች ወደ የከተማቸው የሚደረገው በረራ ላይ እክል ሲገጥም፤ ክልሉ ተመልሶ ጦርነት የሚገባበት አንዱ ምልክት አድርገው በመውሰድ ስጋት ሲገባቸው ቆይቷል።
የስጋታቸው መነሻ ደግሞ በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል በየጊዜው የሚፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት ነው። ከስድስት ዓመት በትግራይ በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ የተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ ወደ ስራ ከተመለሰ በኋላ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡ ውጥረቱን አባብሶታል።
የክልሉን ስራ አስፈጻሚ “አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ” ስራቸውን እንዲቀጥሉ እንዲያደርጉ በምክር ቤቱ ስልጣን የተሰጣቸው ዶ/ር ደብረጽዮን፤ በትላንትናው ዕለት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከተመረጠው ካቢኔ ጋር የመጀመሪያ ስብሰባቸው አድርገዋል። ይህ ስብሰባ እየተካሄደ ባለበት ወቅት፤ በመቐለ ከተማ የጦር ጀት ሲያንዣብብ መታየቱ በማህበራዊ የትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በመቐለ ከተማ የጦር ጀት ሲታይ በዚህ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዓመታት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያው የጀት በረራ በመቐለ የታየው፤ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ስብሰባውን ባደረገበት ባለፈው ማክሰኞ ነበር።
የትላንቱ የካቢኔ ስብሰባን ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ያወጡት መግለጫም፤ በትግራይ ክልል ያለውን የፖለቲካ ውጥረት አባብሶታል። ሌተናል ጄነራል ታደሰ በዚሁ መግለጫቸው፤ የትላንቱ የካቢኔ ስብሰባ “በቀጣይ ወደ አደገኛ መንገድ የሚያስገባ” ሁነት እንደሆነ ገልጸዋል።
“ተመርጫለሁ” በሚል ምክንያት የካቢኔ ስብሰባውን ያካሄደው አካል፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስልጣን “በጉልበት እየያዘ ያለ ኃይል” መሆኑም ሌተናል ጄነራል ታደሰ በመግለጫቸው አመልክተዋል። በዚህ ምክንያት ለሚከተለው ውጤት ተጠያቂው ይኸው ኃይል መሆኑንም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አስጠንቅቀዋል።

በዚህ ፖለቲካዊ ውጥረት መካከል የተከሰተው የዛሬ ጠዋቱ የአውሮፕላን ጉዞ እክል በተጓዦች እና በነዋሪዎች ዘንድ ስጋትን ቢወልድም፤ ጉዳዩ “ከቴክኒክ ችግር” የተያያዘ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል። የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለማ ያደቻ፤ የጠዋቱ አውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ የተደረገው በአሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ “የኮሚኒኬሽን መሳሪያ የቴክኒክ ብልሽት” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
“የመጀመሪያው በረራ ሄዶ ነበር። ሊያርፍ ሲል የመሬት ላይ የኮሚኒኬሽን መሳሪያው አይሰራም ነበር። ስለዚህ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ መጣ። እሱ ከተስተካከለ በኋላ [አውሮፕላኑ] ተመልሶ ሄዶ አርፏል” ሲሉ አቶ ለማ ችግሩ በአውሮፕላኑ ውስጥ የተከተሰተ እንዳልሆነ አብራርተዋል። በጠዋቱ በረራ ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ መንገደኞች፤ በዚያው አውሮፕላን ወደ መቐለ በድጋሚ ተጉዘው በሰላም ማረፋቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































