በነገሌ ምርጫ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች ላይ በመጪው ሐሙስ ምርጫ ሊካሂድ ነው

በሃሚድ አወል 

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፤ ነገሌ ምርጫ ክልል በሚገኙ 30 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በመጪው ሐሙስ ምርጫ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በሰላዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ስለሚደረገው ምርጫ፤ በምርጫ ክልሉ ያሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲያውቁት መደረጉንም ቦርዱ ገልጿል። 

ምርጫ ቦርድ ከሰኔ አስራ አራቱ ምርጫ አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ፤ በነገሌ ምርጫ ክልል በቀረበ አቤቱታ ምክንያት ድምጽ የመስጠት ሂደቱ እንደማይከናወን አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ በዕለቱ 109 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ሲካሄድ ውሎ ነበር። ቦርዱ በምርጫ ክልሉ ድምጽ እንዳይሰጥ ወስኖ የነበረው በቦታው የሚወዳደሩ አንድ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ ስማቸው አለመካተቱትን ተከትሎ ያቀረቡትን አቤቱታ በመቀበል ነበር። 

በምርጫ ክልሉ ያሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች፤ የቦርዱን ውሳኔ ወደ ጎን በማለት በአብዛኞች የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ እንዲሰጥ ማድረጋቸው፤ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎችን አስቆጥቶ ነበር። ምርጫው ከተካሄደ ከሶስት ቀናት በኋላ የብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት መግለጫ፤ በነገሌ ምርጫ ክልል የተካሄደውን ምርጫ “ህገ ወጥ” ሲሉ መጥራታቸው ይታወሳል። ሰብሳቢዋ በምርጫ ክልሉ የተካሄደው ምርጫም ተቀባይነት እንደማይኖረው በወቅቱ አስታውቀዋል። 

የቦርዱ ሰብሳቢ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ደግሞ፤ አቤቱታ ያቀረቡት የግል ዕጩ ተወዳዳሪ “ምርጫው በእኔ ምክንያት መደገም የለበትም” በሚል ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ምክንያት ቦርዱ በምርጫ ክልሉ የተካሄደውን ምርጫ መቀበሉን ጠቁመዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ አርብቶ አደር በመሆኑ፤ ጷጉሜ 1፤ 2013 ምርጫ ይካሄድ ቢባል፤ ነዋሪዎቹ የምርጫ ካርድ በወሰዱበት አካባቢ እንደማይገኙ ቦርዱ ማረጋገጡን ብርቱካን በተጨማሪ ምክንያትነት አንስተዋል። 

ዛሬ ሰኞ ሰኔ 28 ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ፤ በምርጫ ክልሉ ባሉ ቀሪ 30 ምርጫ ጣቢያዎች በመጪው ሐሙስ ምርጫ እንደሚካሄድባቸው ተናግረዋል። “በዚህ ሳምንት ሐሙስ፤ በሰላሳዎቹ ጣቢያዎች ብቻ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን አጠናቅቀን፤ የውጤት ድመራው እስካሁን ከተደረጉ የምርጫ ክልሎች ጋር ተደምሮ በሳምንቱ መጨረሻ እንዲመጣ ለማድረግ ወስነናል” ሲሉ ኃላፊተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)