በሃሚድ አወል
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ንግድ ዘርፍ ማህበር፤ ለመጪው የገና በዓል ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ እንግዶች በስሩ የሚገኙ ሆቴሎች ልዩ ቅናሽ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ። ማህበሩ ጥሪውን ያቀረበው 170 ገደማ ለሆኑ ሆቴሎች መሆኑን የማህበሩ ፕሬዝዳንት አስቴር ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ማህበሩ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ባሰራጨው ደብዳቤ፤ የማህበሩ አባል የሆኑ ሁሉም ሆቴሎች ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ እንግዶች የተለየ ቅናሽ እና አቀባበል እንዲያደርጉ ጠይቋል። ማህበሩ ጥያቄውን ያቀረበው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በታህሳስ መጨረሻ ለሚከበረው የገና በዓል አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ በይፋ መጋበዙን ተከትሎ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ማክሰኞ ያቀረበውን ይህን ግብዣ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስተጋብተውታል። ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብለው ለሚጠበቁ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች፤ “የሀገር ልጅ ጥቅል” በሚል ስያሜ “ከፍተኛ ቅናሾች” እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር በደብዳቤው ጥያቄ አቅርቧል።
እንደ አስቴር ሰለሞን ገለጻ ማህበሩ ሆቴሎች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ቅናሽ እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያቀርብ የመጀመሪያው አይደለም። በአዲስ አበባ በሚካሄዱ መርሃ ግብሮች ምክንያት በርካታ እንግዶች ወደ ከተማይቱ በሚመጡበት ወቅት ማህበሩ ተመሳሳይ ጥሪዎችን ያደርግ እንደነበር ያስረዳሉ። ማህበሩ ለሚያቀርበው የአገልግሎት ቅናሽ እና የተለየ መስተንግዶ ጥሪ ከሆቴሎቹ “ጥሩ ምላሽ” ያገኙ እንደነበርም ገልጸዋል።

የአሁኑ የማህበሩ ጥሪ ለሆቴሎች ከመቅረቡ አስቀድሞ፤ የሸራተን አዲስ ሆቴል ለአንድ ወር የሚቆይ ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል። ከረቡዕ ህዳር 22፤ 2014 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን በተገለጸው በዚህ ቅናሽ፤ ሆቴሉ ከዚህ በፊት ለአገልግሎቱ ከሚያስከፍለው በ13 በመቶ ያነሰ ዋጋ ያቀረበበት ነው።
በኢትዮጵያ መንግስት የተደረገውን ጥሪ ተቀብለው “ዳያስፖራዎች” ወደ ሀገር ውስጥ በብዛት ከገቡ፤ ለሆቴል እና መስተንግዶ ዘርፉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ይናገራሉ። የሆቴል እና መስተንግዶ ዘርፉ በኮሮና ቫይረስ እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ተጎድቶ እንደነበር የሚናገሩት ፕሬዝዳንቷ፤ የአሁኑ አጋጣሚ ዘርፉ “ከደረሰበት ጫና እንዲያገግም ይረዳዋል” ይላሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)