በኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ የሚገኘው ሳፋሪኮም፤ አዳዲስ ምሩቃንን አሰልጥኖ ለሚቀጥርበት ፕሮግራም 130 ሺህ ማመልከቻዎች መቀበሉን አስታወቀ። የኩባንያው የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ሞካያ ሞካያ እንደተናገሩት ማመልከቻቸውን ካቀረቡ የተሻገሩ አዳዲስ ምሩቃን መካከል በስተመጨረሻ የሚቀጠሩት 150ዎቹ ናቸው።
በ100 ሚሊዮን ዶላር ሥራውን የሚከውንበት ግዙፍ የዳታ ማዕከል በአዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ የገነባው ሳፋሪኮም፤ እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ አንድ ሺህ ሰራተኞች እንደሚቀጥር አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ “ዲስከቨር ግራጁዌት ማነጅመንት ፕሮግራም” በተባለው አሰራሩ በሶስት አመታት ውስጥ 450 አዳዲስ ምሩቃንን ይቀጥራል።
ሳፋሪኮም የሚቀጥራቸውን አዳዲስ ምሩቃን በኩባንያው የቢዝነስ ክፍል በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እየተዘዋወሩ ፈጣን ትምህርት ይሰጣቸዋል ተብሏል። የኩባንያው ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶሳ ባለፈው መስከረም ወር እንደገለጹት፤ አዳዲስ ምሩቃኑ ሰፊ የአመራር ስልጠና እና “ሜንቶርሺፕ” ጭምር ይከታተላሉ።
ሳፋሪኮም ቴሌኮሚዩኒኬሽንስ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አስራ ሁለት ከፍተኛ አመራሮቹን በመስከረም ወር ይፋ ካደረገ በኋላ፤ በማስታወቂያ እንዲያመልክቱ ያጋበዛቸውን አዳዲስ ምሩቃንን እስከ ጥቅምት 2014 ሲመዘግብ ቆይቷል። ኩባንያው ለዚሁ መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር ምልመላ ብቻ 130 ሺህ አመልካቾችን መመዝገቡን ዛሬ ሐሙስ ጥር 26 አስታውቋል።
የተመዝጋቢዎቹ ቁጥር “ብዙ እንደሆነ አውቃለሁ” ያሉት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ሞካያ ሞካያ፤ ኩባንያው ለአዳዲስ ምሩቃን ላዘጋጀው መርሃ ግብር የሚሆኑ አመልካቾች የሚመለመልበትን መንገድ አብራርተዋል። “በእጃችን የሚገኙ የተለያዩ ዲጂታል የግምገማ መሳሪያዎችን እንጠቀማለን” ያሉት የሳፋሪኮም የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ፤ በኢንተርኔት አማካኝነት የመጀመሪያው ምልመላ እንደሚያካሄድ ተናግረዋል። ኩባንያው የሚያወጣቸውን “የኦንላየን ምዘናዎችን” የሚያጠናቅቁ እጩዎች በስልክ እና በኢሜይል ጥሪ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ያሸነፈው ሳፋሪኮም፤ ኢትዮ ጆብስ በተባለው ድረ-ገጽ በኩል በርከት ያሉ የሥራ ማስታወቂያዎች አውጥቶ አመልካቾችን በመቀበል ላይ ነው። ኩባንያው የሥራ ማስታወቂያ ያወጣው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ጋምቤላ እና አሶሳ ለመሳሰሉ ዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች ጭምር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)