በሃሚድ አወል
ላለፉት 90 ቀናት በእስር ላይ በሚገኘው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ላይ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ። የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተባለው ጊዜ ክስ እስኪመሰርት ድረስም፤ ጋዜጠኛው በፊንፊኔ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ በሚገኘው ዳለቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ አዝዟል።
የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሁለቱን ትዕዛዞች ያስተላለፈው፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በጋዜጠኛው ላይ ሲያከናውን የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 1፤ 2014 ለተሰየመው ችሎት መግለጹን ተከትሎ ነው። የኦሮሚያ ፖሊስ በዛሬው የችሎት ውሎ የጋዜጠኛውን የምርመራ መዝገብ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማስተላለፉን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ከሁለት ሳምንት በፊት የካቲት 17፤ 2014 በነበረው የችሎት ውሎ “ምርመራዬን አልጨረስኩም” በማለቱ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቅዶለት የደረሰበትን ውጤት ለዛሬ እንዲያቀርብ ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር። ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን የጠየቀው፤ የተጠርጣሪውን “ስልክ፣ ሚሞሪ ካርድ እና ኮምፒዩተሮች ለመመርመር” በሚል ነበር።
የኦሮሚያ ፖሊስ በዛሬው ችሎቱ “ምርመራዬን ጨርሻለሁ” ከማለት ባለፈ በተፈቀደለት 14 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለችሎቱ አለማሰማቱን የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ገመቹ ጉተማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ምርመራውን ማጠናቀቁን ለችሎቱ ከገለጸ በኋላ፤ የጋዜጠኛው ጠበቃ በደንበኛቸው ላይ የተከፈተው የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እንዲዘጋ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
ደንበኛቸው “የተጠረጠረበት ወንጀል ዋስትና የማያስከለክል” መሆኑን ለፍርድ ቤቱ የገለጹት ጠበቃው፤ ይህንን ታሳቢ በማድረግ “ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲጠብቅለት” በተጨማሪነት መጠየቃቸውን አብራርተዋል። የጋዜጠኛው የዋስትና መብት የማይጠበቅ ከሆነ ደግሞ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፤ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንደሚሰርት በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው መጠየቃቸውን አቶ ገመቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ ያቀረቡትን የዋስትና መብት መከበር ጉዳይ የተመለከተው የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ ጥያቄውን ሳይቀበል ቀርቷል። ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ ያደረገው፤ ተጠርጣሪው “በሽብር ወንጀል የተጠረጠረ ስለሆነ የዋስትና መብቱን አልጠብቅም” በሚል ምክንያት እንደሆነ ጠበቃው አስረድተዋል። ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ “ክልሎችን እና የአገር መሪዎችን በማሳነስ ስድብ እና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ” እንዲሁም “አገርን በማሸበር” ወንጀሎች መጠርጠሩን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቀደም ሲል ለፍርድ ቤት ማስታወቁ አይዘነጋም።
የወረዳው ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄውን ባይቀበልም የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንደሚሰርት ግን ትዕዛዝ ማስተላለፉን አቶ ገመቹ ገልጸዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ጥያቄ መሰረትም በጋዜጠኛ ታምራት ላይ ክስ እስኪመሰረትበት ድረስ ተጠርጣሪው በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ዳለቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
“ተራራ ኔትወርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ የሆነው ታምራት ነገራ ታህሳስ 1፤ 2014 በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አብዛኛውን የእስር ጊዜውን ያሳለፈው በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ስር በሚገኘው የገላን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያ ነው። የጋዜጠኛውን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤትም ከፖሊስ ጣቢያው አቅራቢያ የሚገኝ ነው።
የዛሬውን የጋዜጠኛውን የፍርድ ቤት ውሎ ለመከታተል ቤተሰቦቹ በስፍራው ቢገኙም ወደ ችሎት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ጠበቃ ገመቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)